የአልማዝ ዴንታል ላብራቶሪ አዳዲስ የጥርስ ህክምና ቴክኖሎጂዎችን አስተዋወቀ

- Advertisement -
Sidebar AD


#Ethiopia | የአልማዝ ዴንታል ላብራቶሪ የውጭ ምንዛሬን የሚያድንና የጥርስ ህክምና አገልግሎትን የሚያዘምን “ክሊር አላይነር” (Clear Aligner) የተሰኘ የማይታይ የጥርስ ማስተካከያ ቴክኖሎጂን ጨምሮ አዳዲስ ምርቶቹን በዛሬው ዕለት ባከናወነው መርሃ ግብር አስተዋወቀ።

​የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይታየው ተስፋዬ በዕለቱ እንደገለጹት፣ ላብራቶሪው ከተመሰረተባቸው ያለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ የተለያዩ አርቴፊሻል ጥርሶችን ለሀገር ውስጥ ክሊኒኮች ሲያቀርብ ቆይቷል።

አሁን ግን በዋነኝነት “የአልማዝ አላይነር” የተሰኘውንና የተወለጋገዱ ጥርሶችን ያለ ምንም ብረት (Brace) በፕላስቲክ ቁሳቁስ ብቻ ማስተካከል የሚያስችለውን አዲስ ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩን አብስረዋል።

​አቶ ይታየው አክለውም “ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ሀገር ተልኮ የሚሰራ በመሆኑ ለከፍተኛ የዶላር ወጪና ለጊዜ መጓተት ይዳርግ ነበር፤ አሁን ግን በሀገር ውስጥ መመረቱ እነዚህን ችግሮች ከመቅረፉ ባለፈ ለሌሎች ላብራቶሪዎች መፈጠርም አርአያ ሆኗል” ብለዋል።

ድርጅቱ ከአላይነር በተጨማሪ ዚርኮኒያ አይ-ባር (Zirconia I-Bar) እና ሰርጂካል ጋይዶችን ጨምሮ አምስት አዳዲስ ምርቶችን ለገበያ አቅርቧል።

​በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጥርስ ህክምና ባለሙያ ዶክተር መስፍን በበኩላቸው፣ አዲሱ አሰራር “ኢንቪዛላይን” (Invisalign) በመባልም እንደሚታወቅና ዋና ጥቅሙም የሰዎችን የውበት ፍላጎት ከእይታ ውጭ በሆነ መንገድ ማሟላቱ እንደሆነ ገልጸዋል። “የውጭ ምንዛሬን ከማዳኑ ባለፈ፣ በዋጋ ረገድም ተመጣጣኝና ለታካሚዎች ምቾት የሚሰጥ በመሆኑ እኛም በክሊኒካችን አገልግሎቱን ለታካሚዎች ማስተዋወቅ እንጀምራለን” ሲሉ የቴክኖሎጂውን ፋይዳ አስረድተዋል።

​ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያ የዶክተር አቤል ስፔሻሊቲ ዴንታል ክሊኒክ ባለቤት ዶክተር አቤል መሰለ፣ ላብራቶሪው በሀገር ውስጥ መኖሩ በሀኪሙና በቴክኒሻኑ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያቀላጥፈው ተናግረዋል።

ዶክተር አቤል “ቀደም ሲል በዲኤችኤል (DHL) ወደ ውጭ የምንልካቸው ስራዎች ላይ ስህተት ቢኖር ለማስተካከል ሳምንታትን ይፈጅ ነበር፤ አሁን ግን እዚሁ በሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ ስራዎችን ማጠናቀቅ መቻሉ ለታካሚዎቻችን ትልቅ እፎይታ ነው” ብለዋል።

​በመርሃ ግብሩ ላይ ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በተጨማሪ ታዋቂው ህንዳዊ የጥርስ ሀኪም ዶክተር ኤም ኬም በቪዲዮ የታገዘ ሙያዊ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፣ የአልማዝ ዴንታል ላብራቶሪም በቀጣይ የዲጂታል ጥርስ ህክምናን ይበልጥ ለማስፋፋትና አለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደሚሰራ አስታውቋል።

​የአልማዝ ዴንታል ላብራቶሪ ስያሜውን ያገኘው የመስራቾቹን እናት ስም ለመዘከር ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እንደ ዚርኮኒያ፣ ቬነር እና ሪቴይነር ያሉ በርካታ የጥርስ ህክምና ውጤቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።

ጌትነት ተመስገን
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1