ከ13ዐ ሀገራት ጋር ለሚደረገው ውድድር ኢትዮጵያ ተወካይዋን ይፋ አደረገች!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከ”ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ” ድርጅት ጋር በመተባበር በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቬትናም በሚካሄደው 73ኛው የዓለም የቁንጅና ውድድር (Miss World) ላይ ኢትዮጵያን ወክላ የምትሳተፈውን ወ/ሪት ሩት ይርጋለምን በይፋ አስተዋወቀ።

በመላው የሀገሪቱ ክልሎች ከተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች መካከል ተለይታ ለፍጻሜ ከደረሱ 50 እጩዎች ውስጥ አሸናፊ ሆና የተመረጠችው ሩት ይርጋለም፤ በዘንድሮው ውድድር ከ130 በላይ ሀገራት ተወካዮች ጋር ትፎካከራለች።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ ውድድሩ ከግል ተሳትፎ ባለፈ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የመንግስት እውቅና ዝግጅት የተደረገበት “ይህ መድረክ ከቁንጅና ባሻገር የሀገራችንን ባህል፣ ቱሪዝም እና ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለአለም ማህበረሰብ የምናስተዋውቅበት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ መድረክ ነው” ብለዋል።

የውድድሩ ብሔራዊ ዳይሬክተር የሆኑት ገነት ፀጋዬ በበኩላቸው፤ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የውድድሩን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገውና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

አሸናፊዋ ወ/ሪት ሩት ይርጋለም በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት ሲሆን፣ በሙያዋ የቡና ቀማሽ (Coffee Cupper) ነች። በሞዴሊንግ ዘርፍ የስድስት ዓመታት ልምድ ያላት ሲሆን፣ በቅርቡ በፊሊፒንስ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እስከ መጨረሻው ዙር በማለፍ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓ ይታወሳል።

አሸናፊዋ ሩት በቬትናም በሚካሄደውና ከ130 በላይ አገራት በሚሳተፉበት 73ኛው የዓለም የውበት ውድድር (Miss World) ላይ ኢትዮጵያን የምትወክል ሲሆን በዚህም ወቅት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የተፈጥሮ ውበት፣ የብሄርብሄረሰቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ አለባበስ እና ምግብ ለአለም የምታስተዋውቅ ሲሆን በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ከፍተኛ አደራ እንደተጣለባት ነዉ የተገለፀዉ፡፡

ከውበት ባሻገር “ውበት ለበጎ ዓላማ” (Beauty with a Purpose) በሚለው መርህ መሠረት አሸናፊዋ በማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ ላይ እንደምትሰራም የተገለፀ ሲሆን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይም የራሷን አሻራ እንደምታሳርፍ ይጠበቃል።

ወደ ውድድሩ ከመጓዟ በፊት ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ ሩት በንግግር ጥበብ እና በዓለም አቀፍ ተግባቦት ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ስልጠና እንደምትወስድ ተገልጿል። በተጨማሪም የህዳሴ ግድብንና የተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮችን በመጎብኘት ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ስራዋ ግብዓት የምታሰባስብ ይሆናል።

የ73ኛው የዓለም የቁንጅና ውድድር በቅርቡ በቬትናም አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ታሪክትሰራለች ተብሎ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባታል።





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2