የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃን የሚያጠናክር የ18 ወራት ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​ሰላም ኢትዮጵያ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ላለፉት 18 ወራት ሲያከናውን የቆየው የአእምሯዊ ንብረት መብትን የማስከበርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮጀክት መጠናቀቁን አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የሰላም ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መንግስቴ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በተለይ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በስነ-ጽሁፍ እና በሌሎች የፈጠራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የፈጠራ ውጤቶቻቸው በህግ እንዲጠበቅላቸውና ተገቢውን የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻል በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።

​በአዲስ አበባ እና በአምስት የክልል ከተሞች ላይ ሲተገበር የቆየው ይህ “SIPRE” የተሰኘ ፕሮጀክት በዋናነት የህግ አስፈጻሚ አካላት፣ የኪነ-ጥበብ ማህበራት እና ባለሙያዎች ስለ አእምሯዊ ንብረት ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አቶ ሲሳይ አክለውም የኪነ-ጥበብ ስራዎችን መጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን የነበሩት የህግ ማዕቀፎች ከወቅቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር አብረው እንዲሄዱ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ እና ዳኞች የፈጠራ ስራ ስርቆትን እንደማንኛውም የወንጀል ድርጊት አይተው ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ የግንዛቤ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

​በመዝጊያ መርሃ-ግብሩ ላይ እንደተገለጸው፤ ሰላም ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የውል ስምምነት ቅጾችን በማዘጋጀትና ለባለሙያዎች በማሰራጨት የአርቲስቶችን የሞራልና የቁሳቁስ መብት ለማስከበር ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በቀጣይም የተጀመሩ የህግ ማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የሙያ ማህበራት የአባላቶቻቸውን መብት በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀርቧል።

ጌትነት ተመስገን
📷 ጥላሁን ደሳለኝ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1