የመክሊት : የስኬት አርበኛ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የመክሊት 25 ዓመታት ጉዞ ትርጉም የሚኖረው በደጃፋችን ባሉ ስኬታማ ደንበኞች ሕይወት ውስጥ ነው። በዚህ መዝጊያ ምዕራፍ፣ ተቋሙን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ተጠቅመው ከድህነት ወደ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ ስድስት “የስኬት አርበኞችን” እናስተዋውቃችኋለን።

እነ ታየች፣ መነን፣ ጸዳለ፣ አቤልና ለገሰ የመክሊትን ብድር በመጠቀም የፈጠሩት የሥራ ዕድልና ያፈሩት ሀብት የሚደነቅ ነው።

በተለይም እንደ ወይዘሮ ሙሉወርቅ ያሉ ከሻይ ንግድ ተነስተው ፎቅ ያቆሙ እናቶች ታሪክ፣ መክሊት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለውን ተጨባጭ ድርሻ ያረጋግጣል። ይህ ምዕራፍ የቃል ብቻ ሳይሆን የተግባር ምስክርነት፣ የሕልም እውን መሆንና የመክሊት የሩብ ክፍለ ዘመን ትልቁ ትርፍ ነው፡፡

ከ500 ብር ብድር እስከ ሚሊዮኖች መዋዕለ ንዋይ

የወይዘሮ ታየች ፈለቀ
የሩብ ክፍለ ዘመን የጥንካሬና የድል ጉዞ

ወይዘሮ ታየች ፈለቀ ሕይወትን በፈተና ነው የጀመሩት። በ15 ዓመታቸው እናት የሆኑት ታየች፣ ገና በወጣትነታቸው ባለቤታቸውን በአደጋ አጡ። ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው በትምህርትና በንግድ መካከል ሲታገሉ እናታቸውም አረፉባቸው። በዚያ የጨለማ ወቅት ነበር መክሊት “ቤት ለቤት” ግንዛቤ ሲሰጥ የደረሰላቸው።

“እናቴ ሞታብኝ፣ ተስፋ ቆርጬ በነበረበት ወቅት ነው መክሊት የመጣው” ይላሉ። ያኔ በ1993 ዓ.ም የመጀመሪያዋን 500 ብር ሲበደሩ ፍርሃት አልነበረባቸውም። “ብሩን ወስጄ ሠርቼ አተርፍበታለሁ እንጂ አልፈራሁም፤ ባይሆንልኝ እንኳ በልቼው ልሙት በሚል ቆራጥነት ነው የጀመርኩት” ሲሉ ያንን ታሪካዊ ጅማሬ ያስታውሳሉ።

የዕድገት መሰላል፦ ከጠላ ጥመቃ እስከ አይሱዚ መኪና

ያቺ 500 ብር የለውጥ ቁልፍ ነበረች። በጠላና በእንጀራ ንግድ የጀመሩት ታየች፣ ቀስ በቀስ ወደ ከብት እርባታ ተሸጋገሩ። ከአንድ ላም ተነስተው እስከ ሰባት ከብቶች ማርባት ቻሉ። በመካከሉ የእግር መሰበር አደጋና የንግድ መደብዘዝ ቢያጋጥማቸውም፣ መክሊት ዳግም ብድር በመስጠት ከውድቀት

አነሳቸው።

ዛሬ ወይዘሮ ታየች የሦስት ሱቆች ባለቤት ናቸው። ሁለቱን አንድ አድርገው አንዱን ደግሞ መጋዘን አድርገው ይጠቀሙባቸዋል፡ ፡ ከዚህም ባለፈ ለልጃቸው 600 ሺህ ብር ከመክሊት ተበድረው ከራሳቸውም ጨምረው አይሱዚ የጭነት መኪና በመግዛት ከሰው ጥገኝነት አላቀውታል። ጭቃ የነበሩ የቤት ክፍሎቻቸውን አፍርሰው በዘመናዊ መልክ በመገንባት ዛሬ በወር እስከ 50 ሺህ ብር የቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

የገንዘብ አያያዝ ጥበብ፦ “ዋናህን አትብላ”

ለወይዘሮ ታየች ስኬት ትልቁ ምስጢር ጥብቅ የገንዘብ ዲሲፕሊን ነው። “አንድ መቶ ብር ይዘህ የምትገዛበት አስፈላጊ ነገር ካለ፣ ቢርብህ እንኳ በዚያ ገንዘብ መብላት የለብህም፤ ዋናህን መብላት የለብህም” የሚል ፅኑ መርህ አላቸው። ልጆቻቸው እንኳ እናታቸው ገንዘብ እንዳላት በማያውቁበት ሁኔታ፣ በቁጠባና በዕቅድ በመመራት ትልቅ ቤት መገንባትና የሚሊዮን ብር ብድሮችን በአግባቡ መመለስ ችለዋል።
“መክሊት የእናት ጓዳ ነው፤ መክሊት ሕይወቴን የቀየረ፣ መሠረቴና ቤቴ ነው”

መክሊት ለታየች ምንድነው?

ለወይዘሮ ታየች መክሊት ድርጅት ብቻ አይደለም። “መክሊት የእናት ጓዳ ነው፤ መክሊት ሕይወቴን የቀየረ፣ መሠረቴና ቤቴ ነው” ይላሉ። በታመሙበት ወቅት ሠራተኞቹ ቤታቸው ድረስ መጥተው ጉዳያቸውን የሚፈጽሙላቸው መሆኑ ተቋሙ ለደንበኞቹ ያለውን ቅርበት የሚያሳይ እንደሆነ ይመሰክራሉ።
ዛሬ ወይዘሮ ታየች የልጅ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት እያስተማሩ፣ በትርፍ ሰዓታቸው በባልትና ሥራ ተጠምደው በሰላም ይኖራሉ። በ25 ዓመቱ ጉዞ ውስጥ መክሊትና ታየች
አብረው አድገዋል፣ አብረውም ከፍ ብለዋል።





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: