ልባም የኦቲዝም ማዕከል በወላይታ ሶዶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ማዕከሉ ከከተማ አስተዳደሩ ባገኘው ቦታ ላይ የቴራፒና የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት የህዝብና የባለሀብቶችን እገዛ ጠይቋል።

ወላይታ ሶዶ — በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ብቸኛ የሆነው “ልባም የኦቲዝም ማዕከል”፣ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ካሏቸው ወላጆች ጋር በኦቲዝም ግንዛቤ ዙሪያ ያተኮረ ሰፊ የምክክርና የትምህርት መድረክ አካሄደ።

ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የኤፕሪል (ሚያዝያ) የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ፤ ስለ ኦቲዝም ምንነት፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ስላሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዲሁም ልጆች ሊደረግላቸው ስለሚገባ የቴራፒና የእንክብካቤ አይነቶች ለወላጆች ዝርዝር ገለጻ ተደርጓል።

ከተቋቋመ አንድ ዓመት የሞላው ይህ ማዕከል፣ በወላይታ ሶዶና አካባቢው ለሚገኙ ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ተስፋ ለመሆን አልሞ የተነሳ ተቋም ነው።

የማዕከሉ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ለምለም ንጋቱ እንደገለጹት፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደርና ከንቲባ ወ/ሮ እታገኝ ሀይለማሪያም ለማዕከሉ አገልግሎት መስጫ የሚሆን ቦታ በመፍቀድ ላሳዩት አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ የተፈቀደውን ስፍራ ለተሟላ አገልግሎት ምቹ አድርጎ ለመገንባትና ለማዘጋጀት የማዕከሉ አቅም ውሱን በመሆኑ ድጋፍ ፈልገው ወደማዕከሉ ለሚመጡ ወላጆችና ልጆቻቸው የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በከተማው መሀል ጊዜያዊ ቢሮ በመክፈት ስራ የጀመረ ሲሆን፣ አስፈላጊው ድጋፍ ተገኝቶ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ልጆች እንደ የባህሪ ሕክምና (Behavioral Therapy)፣ የንግግር ሕክምና (Speech Therapy)፣የአካላዊ ቅንጅት ሕክምና (Occupational Therapy) ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል፦

ሲስተር ለምለም አክለውም፤ ብዙ እናቶች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደሚታገሉ በመጥቀስ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ማዕከሉን በመገንባትና ስራ በማስጀመር ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች በጋራ ከደገፍናቸው ከጥገኝነት የተላቀቀ ትርጉም ያለው ህይወት መምራት ይችላሉ” ብለዋል፡፡
ማዕከሉን ለመደገፍና ለበጎ አድራጎትና ተግባራት የሚከተሉትን የማዕከሉን የሂሳብ ቁጥሮች መጠቀም የሚቻል መሆኑንም በመግለጫቸው አካትተዋል፡፡

ልባም ኦቲዝም ማዕከል
• የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፦ 1000727042222
• ብርሃን ባንክ፦ 2503240166663
• አድራሻ፦ ወላይታ ሶዶ፣ ሊጋባ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት (ሊጋባ ፔንሲዮን 1ኛ ፎቅ)
• ስልክ፦ 0912149990






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2