የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ 12÷1 “ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አስራ ሁለት የክዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት” ብሎ የመሰከረላት የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ልዩ ናት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢቱ ኢሳ 7፡14 “ድንግል ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ብሎ የተናገረላት ያቺ ድንግል ከቅዱሳኑ ኢያቄምና ወሐና ተወለደች፡፡ እርሷ የተወለደችባት ቀን ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝ 44÷9 “የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ብሎ የተናገረላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘችባት ናት፡፡ የእርስዋም ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን ሲገለጽ የነበረ መሆኑን ቅዱሳን መጽሕፍ በሚገባ ያስረዱናል፡፡

አባቷ ንጉስ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፣ ከአማና ራስ ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የዚህ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸው የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ትንቢቱም ሲፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም በ15 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ” ማርያም ግን ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡ በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል።

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት ቀን እጅግ በደመቀ ስነ ስርዓት የሚከበርበት ዋነኛው ምክንያት ከዳዊት አካል የቀረችልን ንጽሕት ዘር በመሆኗ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ዕለት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ‹‹የመመኪያችን ዘውድ፣ የንጽሕናችንም መሰረት›› ያላት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተወለደችበት ነው፡፡ ጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን በመኃልይ 4÷8 “ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፡ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፡፡” ብሎ እንደተናገረ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሰረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሰሎሞን እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን ስለእመቤታችን የተናገረውን ቃል መፈጸሙን ሲያመሰጠር “የአናብስት ልጅ አልኩሽ” ይላል፡፡

ደግሞም “ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ ተራራ ነዪ፤ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ፤ ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን ፡፡” ይላታል፡፡ እመቤታችንም በሊባኖስ ተራራ እንድትወለድ ምክንያት የሆነው በማሕፀን ሳለች የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሳቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ስለነበር ሐናና ኢያቄም ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሄዱ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ስለነገራቸው እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ስለታላቅ መንፈሳዊ ተልዕኮ ሲባል ከሚያውቁት ቦታ መራቅን፣ ከለመዱት ቀዬ መሰደድን ከእመቤታችን የተረዱት ገዳማውያንም ዓለምን ንቀው ስሟን ስንቅ አድርገው ይመንናሉ። ገዳማቸውን ስንደግፍ ፣ በዓታቸውን ስናጸና የበረከታቸው ተሳታፊ እንሆናለን።

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: