#Fastmereja: ኖህ ሪል እስቴት በእንቁላል ፋብሪካ እና በሴቶች አደባባይ ያስገነባቸውን ከ1,341 በላይ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆች በዛሬዉ እለት ለባለቤቶቻቸው አስረከበ።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ የኖህ ሪል እስቴት መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የቤት ባለቤቶች ተገኝተዋል፡፡
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ የግል ዘርፉ በከተማዋ የልማት እንቅስቃሴ ላይ እያሳረፈ ያለውን አዎንታዊ አሻራ አድንቀዋል።
ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አክለዉም የከተማዋ የወደፊት ራዕይ በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ በግል ዘርፉና በነዋሪው የተቀናጀ ርብርብ የሚሳካ መሆኑን ገልጸው፤ ባለሀብቶች በጥራትና በታማኝነት የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት እንዲያሟሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኖህ ሪል እስቴት መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን በበኩላቸው፣ ኩባንያው ባለፉት 13 ዓመታት ከ11,000 በላይ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ቤቶች ለቤት ፈለጊዎች ማስረከቡን የገለፁ ሲሆን ቃላችንን በመጠበቅ ጥራትና ፍጥነትን መሰረት አድርገን ዛሬ ከ33 በላይ ሳይቶችን በማስረከባችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል።
ኖህ በእንቁላል ፋብሪካ የሚገኘዉ ሳይት በ12,000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ፣ ከ650 በላይ የመኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ሱቆችን የያዘ ግዙፍ መንደር ሲሆን መንደሩ የራሱ የከርሰ ምድር ውሃና ሰፊ የመኪና ማቆሚያ የተካተተበት ሲሆን ኖህ በሴቶች አደባባይ የተገነባዉ ከ160 በላይ ቤቶችን የያዘ፣ ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ (Fully Finished) ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው የተገነቡ መሆናቸዉ ተገልጿል።
ድርጅቱ በዕለቱ ለቤት ልማት ዘርፉ ላሳየው ቁርጠኝነትና ለኖህ ሪል እስቴት ላደረገው ድጋፍ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዩ የምስጋና ስጦታ አበርክቷል።
ኖህ ሪል እስቴት በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ በቦሌ አካባቢ “ቦሌ ሆምስ” የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት መጀመሩን ይፋ ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ በመገናኛ፣ሲኤምሲ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም፣ እንግሊዝ ኤምባሲ እንዲሁም በወሰን አካባቢዎች በአጠቃላይ 3,000 ቤቶችን ለማስረከብ መታቀዱ ተገልጿል።
ኖህ ሪል እስቴት ከ2019ዓ.ም እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አቅም ያገናዘቡ 25,000 የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ግዙፍ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡



Source: FastMereja









No comments yet.