ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት በቀረበው የአሜሪካ የስምምነት ዕቅድ ላይ የኢራንን ምላሽ ለማግኘት እየጠበቁ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናገሩ።
አሜሪካ ባለ 14 ነጥብ የስምምነት ዕቅድ አዘጋጅታ ወደ ኢራን መላኳ የተሰማው በዚህ ሳምንት ነበር። የመግባቢያ ስምምነት እንደሚሆን የተገለጸው ይህ ሰነድ ከያዛቸው ነጥቦች መካከል ኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ስለማድረግ የሚለው ይገኝበታል።
ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ማንሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ነጻ ጉዞን መመለስም ተካትተዋል። በመጨረሻ ይደረሳል ተብሎ የሚጠበቀው የሰላም ስምምነት የሚመሠረተው በዚህ ዕቅድ ውስጥ በተካተቱት ነጥቦች ላይ እንደሚሆንም ተዘግቦ ነበር።
ኢራን ዕቅዱን እየገመገመች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት ሐሙስ ምሽት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
ትናንት አርብ ምሽት ኢራን ለዕቅዱ ምላሽ ሰጥታ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፤ “ምናልባት ዛሬ ምሽት [ምላሻቸውን] እንሰማለን” ብለዋል።
ኢራን ሆን ብላ ድርድሩን እያጓተተች ነው ብለው ያምኑ እንደሆን የተጠየቁት ትራምፕ፤ “አላውቅም” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። “በቅርቡ እናውቃለን” ሲሉም አክለዋል።
ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው ሰዓታትን አስቀድሞም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን ዛሬ ምላሽ ትሰጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረው ነበር።
ሚኒስትሩ ጣሊያን ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ምላሻቸውን ዛሬ የሆነ ሰዓት ላይ እንሰማለን ብለን እንጠብቃለን. . . ምላሻቸውም የምር እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ግን ኢራን ምላሽ ስለመስጠቷ አልተረጋገጠም።










No comments yet.