በወራቤ ስኬታማ የልብ ቀዶ ሕክምና ላደረጉ ባለሙያዎች ምስጋና ቀረበ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja: በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ታሪክ ውስጥ ቀዳሚና ዘመናዊ አሠራርን በማስተዋወቅ የሚታወቀው የታዝማ (TAZMA) የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል፣ የነፃ ሕክምና ዘመቻ እውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር በዛሬዉ እለት በቦሌ ማዶ ሆቴል አካሄደ።

ይህ የእውቅና መርሃ-ግብር በቅርቡ በወራቤ ኮንፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተከናወነው 4ኛው ዙር የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና ዘመቻ ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ምስጋና የቀረበበት ነዉ።

ይህ ዘመቻ ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ የልብ ቀዶ ሕክምና በማከናወን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችም ሕይወት አድን አገልግሎት በነፃ መስጠት የተቻለ ሲሆን ይህም የልብ ሕክምናን በዋና ከተማው ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው አለማየሁ እንደገለጹት፣ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከ16 ዓመታት በፊት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ”አዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል” የተሰኘውን የመጀመሪያውን የግል የልብ ሕክምና ማዕከል በመመሥረት በሀገሪቱ የሕክምና ዘርፍ የማይቻለውን ያስቻሉ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ናቸዉ ሲል ተናግሯል።

ዶክተሩ ሕክምና ከመስጠት ባለፈ፣ በርካታ የኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሐኪሞች በራሳቸው ወጪ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲሰለጥኑ በማድረግ ለእውቀት ሽግግርና ለትውልድ ግንባታ የላቀ ሚና መጫወታቸው በዝርዝር ተመላክቷል።

ታዝማ የዶክተር ፍቅሩን ራዕይ ይበልጥ ለማስፋትና የሕክምና አገልግሎቱን ለማዘመን አዲስ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች የተሟላ ግዙፍ ሆስፒታል በግንባታ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ማዕከሉ፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ የልብ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ ውስብስብ የሕክምና አገልግሎቶችን በጥራት፣ በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።

በተጨማሪም ማዕከሉ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በሀዋሳ፣ በጋምቤላና በወለጋ የጀመረውን ነፃ የሕክምና አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

ተቋሙ ከጥቁር አንበሳና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች እንዲሁም ከሌሎች የመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: