ከ88 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን አንድ ሪፖርት አመለከተ

- Advertisement -
Sidebar AD

በኢትዮጵያ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ትዝብት ካደረጉባቸው ጣቢያዎች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ሕብረት ለምርጫ ባካሄደው ጉብኝት ማረጋገጡን አስታውቋል።

ሕብረቱ በ4 ሺህ 396 የምርጫ ጣቢያዎች ባካሄደው ቅኝት የደረሰበትን ድምዳሜ ሪፖርት አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ፡- ምዝገባው ከተከናወነባቸው ስፍራዎች መካከል በሕግ ከተፈቀደው ውጭ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በሃይማኖታዊ ተቋማት እና በመጠጥ ቤቶች የተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን ገልጾአል።

የሕብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለማርያም ለአሐዱ ሬድዮ እንደገለጹት፤ አብዛኞቹ የምዝገባ ጣቢያዎች በተገቢው ስፍራ ቢቋቋሙም፣ ሕጉን ባልተከተለ መልኩ የተመሰረቱ ውስን ጣቢያዎች መኖራቸውን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ጣቢያዎቹ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በሚመች መልኩ አለመዘጋጀታቸውን በጥናት ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

የምዝገባ ሂደቱ በአብዛኛው መልካም መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ 87 በመቶዎቹ ጣቢያዎች የመራጮችን ማንነት በአግባቡ በመለየት ቢመዘግቡም፣ ቀሪዎቹ 13 በመቶዎቹ ግን መመሪያውን ሳይከተሉ መመዝገባቸውን አስረድተዋል። በተጨማሪም በጥቂት ስፍራዎች ላይ ሰዎች በአካል ሳይገኙ ምዝገባ መከናወኑን ህብረቱ በትዝብቱ ማረጋገጡን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል አሐዱ የሕግ ጥሰት በተፈጸመባቸው ጣቢያዎች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሰብሳቢዋ በሰጡት ምላሽ ቦርዱ የሕግ ጥሰት ተገኝቶባቸዋል ባላቸው በ5 ክልሎች በሚገኙ 23 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የእግድ እርምጃ መውሰዱን መግለጻቸው ይታወሳል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. የመራጮች ምዝገባ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሂደቱም ለተጨማሪ ሰባት ቀናት ተራዝሞ ቆይቷል። ቦርዱ ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፤ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን አስታውቋል።

አሐዱ ሬዲዮ



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: