#FastMereja I በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት፣ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲና የፕሮግራም ክርክር ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሄደ። በመድረኩ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በልማት ፖሊሲዎች፣ በሀገራዊ ጥቅምና ፍላጎቶች ዙሪያ የየራሳቸውን አማራጭ ሃሳቦች አቅርበዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ወቅት መድረኩ ሙሉ በሙሉ አካዳሚያዊ፣ ገለልተኛና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደሚመራ አረጋግጠዋል። ዜጎች ሉዓላዊ ፍቃዳቸውን ተጠቅመው መፃኢ እድላቸውን የሚወስኑበት ወቅት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አስራት፣ ታዳሚው የቀረቡትን ሃሳቦች በሂሳዊ መንገድ እንዲመረምር አሳስበዋል።
የስትራቴጂና ወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት ክፍል አስተባባሪ አቶ ሀቢብ ሰይድ በበኩላቸው፣ ዳይሬክቶሬቱ ሀገራዊ ጉዳዮችን በገለልተኝነት የመመርመርና ስትራቴጂካዊ አማራጮችን የማመንጨት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት “የውይይት ባህል ለሀገር ግንባታ” እና “የውክልና ዲሞክራሲና የምርጫ ስርዓት” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምሁራዊ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በአቶ ጀምበሩ አረጋ አወያይነት በተመራው የፓርቲዎች ክርክር፣ ተወካዮቹ ከታዳሚዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩም መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በሰላም ተጠናቋል።



Source: FastMereja









No comments yet.