የቡና ስኮላርሺፕ በከፍተኛ ውጤት ለተመረጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ አበረከተ

- Advertisement -
Sidebar AD


#Ethiopia | ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመው “የቡና ስኮላርሺፕ” ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡና ልዩ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች አወዳድሮ የእውቅናና የትምህርት ድጋፍ የመስጠት መርሃ-ግብር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አካሄደ።

በስዊድንና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተመሠረተው ይህ ተቋም፣ በከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ያለፉ ተማሪዎች ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችላቸውን ወሳኝ የገንዘብና የማማከር ድጋፍ አድርጓል።

​በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቡና ስኮላርሺፕ መስራችና የጃታኒ አሊ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሚሊቻ ሎጄ፣ ፕሮጀክቱ “ቡና” የሚለውን ስያሜ የያዘው በምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። ቡና በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ሰዎችን የማገናኘት፣ ችግሮችን የመፍታትና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተሩ፣ ስኮላርሺፑም ተማሪዎችን ከዓለም አቀፍ ዕድሎች ጋር በማገናኘት ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ ለመሥራት መነሳቱን ገልጸዋል።

ድርጅቱ በስዊድንና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን በማነጋገር ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረጉንም አክለዋል።

​የፕሮጀክቱ መስራች አጋርና በስዊድን ነዋሪ የሆኑት ባለራዕዩ ስራ ፈጣሪ አቶ ቢኒያም ፍቃዱ በበኩላቸው፣ ዕለቱ ተራ ሽልማት የሚሰጥበት ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጽናትና ህልም የሚከበርበት መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ቢኒያም “በአንዲት ትንሽ መንደር ያለ ተማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ዕድል የሚያገኝባትንና ተሰጥኦ በገንዘብ እጥረት የማይታፈንባትን ሀገር መፍጠር እንፈልጋለን” ሲሉ ገልጸው፣ ይህ እንቅስቃሴ ለትምህርትና ለተስፋ የሚደረግ ትልቅ ንቅናቄ በመሆኑ በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች፣ የንግድ ማህበረሰቡና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የዚህ ታሪካዊ ራዕይ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

​በዕለቱ የድጋፍ ሰርቲፊኬት ከተረከቡት ተማሪዎች መካከል ዮሐንስ ደበሳይ የተባለው ተማሪ በሰጠው ምስክርነት፣ በታዋቂው የስዊድን ኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍያ ተሸፍኖለት የነበረ ቢሆንም፣ የኑሮ ወጪውን ለመሸፈን በመቸገሩ ትምህርቱን የመጀመር ህልሙ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አስታውሷል። የቡና ስኮላርሺፕ ያደረገለት ድጋፍ ይህንን ትልቅ መሰናክል በመቅረፍ ህልሙን እውን እንዳደረገለት በደስታ ገልጿል።

ከእሱ በተጨማሪም ተመስገን አዲሱ፣ ሳምሶን ፀጋዬና ኃይለአምላክ ገብረኢየሱስ የተባሉ ተማሪዎች በላቀ ውጤታቸውና ለማህበረሰቡ ባሳዩት ቁርጠኝነት ተመርጠው የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።

​የቡና ስኮላርሺፕ በዚህ ዙር ማመልከቻ ካስገቡ 394 ተማሪዎች መካከል ውጤትን፣ የሥራ ልምድን፣ ስብዕናንና ለማህበረሰቡ የተደረገ አስተዋጽኦን መሠረት በማድረግ የምርጫ ሂደት ማካሄዱን አስታውቋል።

ተቋሙ ወደፊትም ከ800 በላይ ከሚሆኑ በመላው አለም ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማስፋት፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘመናዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ ቀስመው ወደ ሀገራቸው በመመለስ በጤና፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለውጥ እንዲያመጡ የመሥራት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: