በኤራን ዩራንየም ጉዳይ ሩስያ ድጋፍ የማድረግ ሃሳብ ማቅረቧን ኢራን አረጋገጠች

- Advertisement -
Sidebar AD

ኢራን ከምዕራቡ ዓለም ጋር በሚያወዛግባት በኒዩክልየር ጉዳይ ላይ ሩስያ የበኩሏን ድጋፍ የማድረግ ሃሳብ እንዳቀረበች ኢራን አረጋገጠች። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ ዛሬ ኒውዴልሂ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሩስያ ጉብኝታቸው ወቅት ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስለ ዩራንየም ጉዳይ መነጋገራቸውን ገልጸው፤ ድጋፍ ለመስጠት ላቀረቡት ሀሳባቸውም አመሰግናቸዋለሁ ብለዋል።

ከብሪክስ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን አራግቺ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ፑቲን በቅርቡ ስለዚሁ ጉዳይ የተናገሩትን አረጋግጠዋል። ፑቲን ባለፈው ሳምንት ሀገራቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጎናጸፈችው ድል በተዘከረበት የመታሰቢያ እለት ሩሲያ በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየምን ከኢራን ወስዳ ለማከማቸት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀው ነበር።

የኢራን የኒዩክልየር መርሀ ግብር ሲያወዛግብ ብዙ ዓመታት አስቆጥሯል። ዩናይትድ ስቴትስ እሥራኤል እና ምዕራባውያን ሀገራት ቴህራን የኒዩክልየር ጦር መሣሪያዎችን ለማምረት ትፈልጋለች ሲሉ ይከሷታል። ኢራን ግን ይህን ታስተባብላለች። ምዕራቡ ዓለም ኢራን አሁን ያላት የዩራንየም ክምችት ከለማ በርካታ የኒዩክልየር ጦር መሣሪያዎች ለመስራት በቂ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሚገኘው ዩራንየም ከሀገሪቱ እንዲወጣ ግፊት እያደረጉ ነው። ዩራንየሙ ከምድር በታች ከሚገኙ የኢራን የኒዩክልየር ተቋማት በአንዱ ውስጥ ተከማችቷል ተብሎ ይገመታል።

DW Amharic



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: