በዚህ መንገድ ተነግሯችሁ ፣ተረድታችሁትስ ታውቃላችሁ ?

- Advertisement -
Sidebar AD

(መላኩ ብርሃኑ)

ኦቲዝም ሰዎች እንደሚያስቡት ዝም ብሎ “ልዩ” መሆን ብቻ አይደለም! ዝም ብሎ ያልተለመደ “እንግዳ ፀባይ” ማሳየትም ብቻም አይደለም።

አንዳንዴ Autism ከዛም በላይ እጅግ የጠለቀ ነው:: ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ውስጣቸው እጅግ ጩኸት የበዛበት ነው። ያ ጩኸት አቅምን የሚፈታተንና መቼ ምን እንደሚፈጠር የማይታወቅበት፥ ስሜትን የሚያጥለቀልቅ ከባድ ማዕበል ነው።

እኛ በቀላሉ የምናልፋቸው ቀላል ነገሮች ነገሮች ለእነሱ የዕለት ተዕለት አድካሚ የትግል ሜዳዎች ናቸው።

ድምፆች ልክ እንደ አካላዊ ህመም ሲሰሟችሁ አስቡት። ከፍተኛ የቦምብ ፍንዳታ ስትሰሙ ከምትሆኑት ነገር ጋር አነጻጽሩት።

እኛ ቸል የምንለው ‘ቲክ ቲክ’ የሚለው የሰዓት ድምጽ ፥ የመኪና ጡሩምባ፥ ወይም የሰዎች ጫጫታ ለእነሱ ልክ ጆሮ ላይ እንደሚጮህ ስፒከር አእምሮን ሲበጠብጠው ይታያችሁ። እንዲያ ነው የሚሰማቸው። የሚጮኸው የጁስ መፍጫ፣ የሚንጫጩ ሰዎች በነሱ አዕምሮ ውስጥ ሲደርሱ በብዙ መቶ እጥፍ ጨምረው ማብቂያ የሌለው ረብሻ ይፈጥራሉ። ከዚያ ለመሸሽ የሚገቡበት ሲጠፋቸው፣ ጆሯቸውን ሲይዙ ስታዩ በነሱ ቦታ ራሳችሁን ተመልከቱ።

ድምጽ ብቻ አይደለም፣ ብርሃን አይንን አጥበርብረው ህዋሳትን ሲረብሹ አስቡት። እኛ የለመድነው የፀሀይ ብርሃን ወይም የክፍላችን አምፑል አይንን እንደሚያቃጥል ፍም ሲሆንባቸው አስቧቸው። ልክ በጨለማ ቤት ውስጥ ድንገት ሃይለኛ ፓውዛ መብራት ሲለቀቅባችሁ እንደሚሰማችሁ ከባድ ህመም ። 💔

ሀሳቦች ከቃላት በላይ ዐዕምሮ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሲጋልቡ… ጭንቅላት ውስጥ ሺ ሀሳቦች በአንድ ጊዜ ሲጋጩ፥ ነገር ግን አንዱንም አውጥቶ ለመናገር አንደበት ሲታሰር አስቡት።

እናንተ በሰማችሁት መጥፎ ዜና ሳቢያ በከፍተኛ ጭንቀትና ግራ መጋባት ውስጥ ሆናችሁ ሁሉም ነገር ሲዞርባችሁ፣ ማሰብ ሲሳናችሁእንደምትሆኑት ለነርሱ ሁሉም ነገር የሚያልፈው በዚያ ሁኔታ ነው። ያኔ ማምለጥ ይፈልጋሉ፣ እረፍት አልባ ሩጫ፣ ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ትርጉም አልባ ድምፆች ያወጣሉ። በዚህ የውስጥ ትርምሳቸውን ያረግባሉ።

የሚነኩት ነገር ልስላሴ ወይም ሻካራነት በቆዳቸው በኩል አልፎ ዐምሯቸው ውስጥ ህመም እንደሚፈጥርስ አስባችሁ ታውቃላችሁ? አይጥ የምትፈሩ ሰዎች አይጥ በእጃችሁ ብትነኩ የሚሰማችሁን ስሜት ትገምታላችሁ አይደል? ለነዚህ ልጆች አንዳንድ ነገሮች እንዲዚያ ናቸው፣ ይረብሻሉ።

ዓለም አንድም እንኳን ረጋ የማትል ስትሆን፣ እንደአውሎ ነፋስ ፍጥነት ሁሉም ነገር ውልብልብ ብሎ መያዝ ሲያስቸግር ፣ .. ሁሉም ነገር ወደዐዕምሮ በአንድ ጊዜ ሲመጣ፥ ዐዕምሮ መረጃዎችን አጣርቶ ቦታ ቦታ ለማስያዝ እጅግ ሲጨነቅ አስቡት። 💔

ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ይሄ ሁሉ የውስጥ ጦርነትና የህዋሳት ጫና (Sensory Overload) በውስጣቸው እየተካሄደ ከዚያ ለማምለጥ ሲታገሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፣ የሚሆኑትን ሁኔታ እንደረብሻ እንቆጥረዋለን። … ምንም እንዳልተፈጠረ “ረጋ በል ! ” “ዝም በል !” “ስርዓት ያዝ !” “አታስቸግር !” “አትቁነጥነጥ” ብለን አጭር ትዕዛዝ እንሰጣቸዋለን።

እስኪ ለአንድ ሰከንድ አስቡት… አንድ ኦቲዝም ያለበት ልጅ ይህንን ሁሉ እረፍት የሚያሳጣ ስሜት በውስጥ ተሸክሞ፥ ማዕበሉን ብቻውን እየታገለ፥ ግን ደግሞ ያንን ስሜት የሚገልፅበት ቃል ሲያጣ! … “እባካችሁ ተቸግሬያለሁ፣ ይህ ነገር አልተመቸኝም፣ ተዉኝ! ” ማለት ሳይችል ሲቀር!

እንደዚህ ያሉ ልጆችን አብዝቶ መታገስ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው! ለእንዲህ አይነት ልጆች ደግነት በጣም ብዙ ትርጉም ያለው ለዚህ ነው! ❤️

ጭንቀታቸውን፣ ያንን ጭንቀት ለማምለጥ የሚያደርጉትን መቅበጥበጥ፣ መሯሯጥ፣ መግቢያ ሲያጡ የሚሆኑትን ነገር መረዳት ብዙ ነገራቸውን ይቀይርላቸዋል !

እኛ የምንሰጣቸው ትንሿ መረዳት፥ ለእነሱ ከሚያስጨንቃቸው ዓለም ለማምለጥ ትልቅ ማረፊያ ትሆናቸዋለች:: ❤️‍

ምክንያቱም ኦቲዝም እንደ ደም መፍሰስ ወይም እንደ ስብራት ጉዳቱ በአይን በማየት ሊገለጽ አይችልም ። በእነሱ ዘንድ እኛ ከምንገምተው በላይ እጅግ በጣም ጠልቆ የሚሰማ የዕለት ተዕለት የውስጥ ረብሻ አለ ❤️‍

ኦቲዝም በሽታ አይደለም!

ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ዓለምን የሚረዱት፣ መረጃን የሚያስተናግዱት እና የሚማሩት ከተለመደው በተለየ (Neurodivergent) መንገድ ነው ።

ሲበሉ፣ ሲጫወቱ፣ ሲፈልጉ በአጠቃላይ አለምን የሚረዱበትም፣ ሚተረጉሙበትም፣ የሚኖሩበትም መንገድ እኛ ከለመድነው የተለየ ነው።

ለመረዳት መሞከርና እነሱን ማገዝ እንጂ ያለልምምድ እና ስልጠና በራሳቸው ተነስተው ወደኛ አለም እንዲመጡ መቆጣት፣ ማመናጨቅ፣ ባስ ሲልም መምታት ተገቢ አይደለም።

የእነሱ የተለየ መሆን የኛን ዓለም ይበልጥ ውብ ያደርጋታል!!

እባካችሁ ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች ከመፍረድ ይልቅ ይበልጥ ጠጋ ብለን ልንረዳቸው እንሞክር ።

ዛሬ ይህንን መልዕክት ማየት፥ መስማት እና መረዳት ያለበት አንድ ሰው ይኖራልና፣ ጽሁፉ ስለ ኦቲዝም ትንሹም ቢሆን ግንዛቤ ከሰጣችሁ Share በማድረግ ለሌሎችም አጋሩ።

(ማስታወሻ! ይህ ጽሁፍ እስካሁን ኦቲዝምን በተመለከተ ከተጻፉት ሁሉ የላቀ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ጸሃፊውን ባላውቀውም ኢንተርኔት ላይ አግኝቼው አብራርቼና አሻሽዬ ጽፌዋለሁ። ወደናንተ ደርሶ የኔ ስሜት ተጋብቶባችሁ ከሆነ ተሳክቶልኛል)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: