ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ፍጹም ህጋዊ መሆኑን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህ ጥያቄ በዓለም ላይ በብዛት ህዝብ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለምትሰለፈው ኢትዮጵያ ተገቢና ምክንያታዊ መሆኑንም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት የገለጹትን አቋም ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ጉዳዩ አሁንም ቢሆን መሰረታዊና ህጋዊ ጥያቄ ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የህዝብ ቁጥር እና የአገሪቱ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እንደ ዋነኛ ምክንያት ጠቅሰዋል።
በርካታ ታዛቢዎች እንደሚስማሙት፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ፣ ከጥንታዊ ስልጣኔዋ፣ ከሀገረ መንግስት ምስረታዋ ፣ ከብሄራዊ ደህንነትና ከረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ግቦች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው።
ኢትዮጵያም ይህንን መልክዓ-ምድራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሰረት በማድረግ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በአጋርነት መርህ ላይ የተመሰረተ የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለጋራ ልማት የሚረዱ ውይይቶችን ስታካሂድ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን በተመለከተ ያላትን ሉዓላዊ መብት ለማረጋገጥ፣ በትውልዶች መካከል የተሸጋገረውን ይህን ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊና በህጋዊ መንገዶች መፍትሄ እንዲያገኙ እየሰራች ትገኛለች።
አምባሳደር አሌክሲ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለመፍታት የሚደረጉ ገንቢ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ፈረንሳይ የምታበረክተው ማንኛውም እገዛ ካለ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎቱ አለን ብለዋል።











No comments yet.