ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በኢትዮጵያውያንና ሌሎች የአፍሪቃ አገራት ዜጎች ላይ የበረታው ሥጋት

- Advertisement -
Sidebar AD

የደቡብ አፍሪቃ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ደርባን ከተማ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ከጸረ ፍልሰተኞች ጥቃት ተጠልለው የነበሩ 400 ግድም የውጭ ዜጎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች አዘዋወሩ ። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የመጤ ጠል እንቅስቃሴ አራማጆች እና ነውጠኞች በፈጠሩት ብርቱ ሥጋት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪቃ አገራት ዜጎች ሕይወታቸውን ጭምር አጥተዋል ። ፖሊስ በከተማዪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ለቀናት በሥጋት ተውጠው ከተጠለሉበት ቦታ በአውቶቡስ ጭኖ ያጓጓዛቸው 400 ግድም ስደተኞች፦ የኢትዮጵያውያ፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ርዋንዳ እና ሶማሊያ ዜጎች መኾናቸውን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ።

በአካባቢው የነበሩ መጤ ጠል አራማጆች፦ «መባረር አለባቸው» እያሉ ሲጮሁ መስማቱን የዜና ምንጩ አክሎ ዘግቧል ። ኾኖም አውቶቡሱ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሕጋዊ ሠነዶቻቸውን በአውቶቡሱ መስኮቶች ሲያሳዩ መመልከቱንም የዜና ምንጩ ጠቅሷል ። መንግሥት ዕውቅና ያልሰጠው የአካባቢው ነዋሪዎች እና አራማጆችሠነድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ከደቡብ አፍሪቃ እንዲወጡ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ የቀረው አንድ ወር ከሳምንት ግድም ብቻ ነው ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የጋና መንግሥት ከ800 በላይ ዜጎቹን ከደብብ አፍሪቃ ለማስወጣት መዘጋጀቱን ትናንት ሐሙስ ይፋ አድርጓል ። የጋና መንግሥት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው አንድ ጋናዊ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ከፍተኛ መነጋገሪያ ከኾነ እና ቁጣ ካጫረ በኋላ ነው ። ደቡባዊ አፍሪቃ በሚኖሩ የዉጪ ዜጎች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት በተመለከተ የአፍሪቃ ኅብረት ኹነኛ ዉሳኔ እንዲያሳልፍም ጋና ጠይቃለች። በደቡብ አፍሪቃ በተለይም በምርጫ ሰሞን ፖለቲከኞች ከሚያራምዷቸው ቅስቀሳዎች ጋር ተዳምሮ መጤ ጠል እንቅስቃዎች እየበረቱ የበርካቶችን ሕይወት መቅጠፋቸው በተደጋጋሚ ይከሰታል ።

DW Amharic




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: