በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ እና የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ2 ሺሕ 400 በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸውንና በአጠቃላይ ጉዳት የደረሰበት የማኅበረሰብ ክፍል ቁጥር ከ17 ሺሕ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የጋሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለአሐዱ አስታውቋል።
ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው አደጋ የ31 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ከፍተኛው ጉዳት የደረሰው 25 ሰዎች ሕይወታቸውን ባጡበት በጋጮባባ ወረዳ መለስ ቀበሌ መሆኑን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ስለሺ ሲሳይ ገልጸዋል።
አደጋው እስከ ግንቦት መጀመሪያ ሳምንት ድረስ በገረሴ፣ በአርባምንጭ ዙሪያ እና በምዕራብ አባያ ወረዳዎች ላይ ተጨማሪ መፈናቀልና ውድመትን ማስከተሉንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
ማኅበሩ አደጋው ከተከሰተበት ሰዓት ጀምሮ አስቸኳይ የምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክምና ድጋፎችን ሲያቀርብ መቆየቱን የገለጹት አቶ ስለሺ በተለይም ውድመት ለደረሰበት የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የላንቴ ጤና ጣቢያ የ1 ሚሊዮን ብር የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት ለቀጣይ አራት ወራት የሚቆይ የ43 ሚሊዮን ብር የረድኤት ፕሮጀክት ይፋ ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱንና በዚህም ለ500 አባወራዎች በየወሩ የ11 ሺሕ 350 ብር የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የውኃ መስመር ጥገና፣ የሳኒቴሽንና የስነ-ልቦና ድጋፎች እየተሰጡ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በመሆኑ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከዞኑ የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል እና ከመንግሥት አካላት ጋር ሰፊ እቅድ እየተነደፈ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በመንግሥት በኩል በቀጥታ ቤት ሊገነባላቸው የሚገቡ 427 አባወራዎች የተለዩ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 100 የሚሆኑትን በምዕራብ አባያ ወረዳ ሁለት ቀበሌያት ላይ ለማስፈር የቦታ ዝግጅት ተጠናቆ የቤት መስሪያ ቁሳቁሶች በአጋር አካላት እየቀረቡ መሆኑን አቶ ስለሺ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም ተጎጂዎችን በዘላቂነት መልሶ በማስፈሩ ሂደት ላይ በቀጥታ ለመሳተፍ ለዋናው ማኅበር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አሳስበዋል።
በ ወልደሐዋርያት ዘነበ

Source: Yeneta Tube









No comments yet.