በመጪው ሰኞ የሚካሄደዉን ሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫን የሚታዘቡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን ኅብረቱ አስታወቀ።
በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የኅብረቱ ታዛቢዎች ከ37 አገራት የተውጣጡ እና 73 አባላትን የያዘ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
የአፍሪካ ኅብረት ማክሰኞ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫው ዕለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን እና ቆጠራን ለመታዘብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሰማሩ መሆኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቱ ሰኞ ግንቦት 24 የሚደረገውን ሰባተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ከአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች በተጨማሪ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢዎች እንደሚገኙ አስታውቋል።
የአፍሪካ ብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ መሠረት መሆኑን የምርጫ ቦርድ እና ኅብረቱ አስታውቀዋል።
የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ግምገማውን በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ፣ በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በተቀመጡ መስፈርቶች ላይ በመመሥረት ግምገማውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ታዛቢዎቹ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዕጩዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ከሌሎች የምርጫ ታዛቢዎች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
ታዛቢ ቡድኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ግንቦት 26/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የሚያደርግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጨረሻ ሪፖርቱን ደግሞ ከምርጫው በኋላ በሁለት ወር ውስጥ ያቀርባል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ከ500 በላይ የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን ማሰማራታቸውን አስታውቀዋል።
Source: Yeneta Tube








No comments yet.