ኮሜርሺያል ኖሚኒስ የ60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ዘመናዊ የሥልጠና ማዕከል አስመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​በሀገራችን የውጭ አቅም የሥራ ዘርፍ ውስጥ ቀዳሚ ስም ያለው ኮሜርሺያል ኖሚኒስ፣ የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በደመቀ ሁኔታ እያከበረ ይገኛል። ተቋሙ ይህንን ታሪካዊ ጉዞውን ምክንያት በማድረግ፣ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት ጥራትና የሰው ኃይል ብቃት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል የተባለለትን ዘመናዊ የሥልጠና ማዕከል በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

​በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኮሜርሺያል ኖሚኒስ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢንተርናሽናል ባንኪንግ ም/ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዮናስ ልደቱ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

​ይህ አዲስ የተመረቀውና የአገልግሎት ልህቀትን ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀው ማዕከል ፣ በዘመናዊ መሠረተ-ልማቶች የተሟላ መሆኑ ተገልጿል። ማዕከሉ ያካተታቸው ዋና ዋና ክፍሎች፦

​በ1 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 580 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ያላቸው ባለ G+4፣ G+2 እና G+1 ሕንጻዎችን ይዟል።

​ሰፊ የሥልጠና ክፍሎች፣ ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፌቴሪያ እና የተግባራዊ ሥልጠና ማሳያ ክፍሎች ተዘጋጅተውለታል።

ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የዋይፋይ ኢንተርኔት፣ ዘመናዊ ፕሮጀክተሮች፣ የድምፅ መሣሪያዎች ፣ የደህንነት ጥበቃ ሥርዓት እና የኃይል ማቋረጥን ለመከላከል የሚያስችል ጄነሬተር አለው።

​ኮሜርሺያል ኖሚኒስ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 32 ቅርንጫፎቹ አማካኝነት ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ግዙፍ ተቋም ነው። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮማንደር ጥላሁን ጸጋዬ ባደረጉት ንግግር፤ ማዕከሉ በቴክኒክ ክህሎት ላይ ብቻ ሳይወሰን በሥነ-ምግባር፣ በደንበኛ አያያዝ እና በአመራር ብቃት ላይ ያተኮሩ ሁለንተናዊ ሥልጠናዎችን በጥራት ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።

​በተለይም በሀገሪቱ እየታየ ካለው ፈጣን የከተሞች ዕድገት፣ የፋይናንስና የኢንዱስትሪ መዋቅሮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ብቁና ታማኝ የሆኑ የጥበቃ፣ የጽዳትና የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያዎች ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ይህ ማዕከል ያንን ክፍተት በመሙላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

​ማዕከሉ ለኮሜርሺያል ኖሚኒስ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ለግል ድርጅቶችና ለባለድርሻ አካላት ጭምር ክፍት ሆኖ መዘጋጀቱ ተበስሯል። ተቋሙ በሀገሪቱ የአውትሶርሲንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ አቅምና ጥራት ለመፍጠር ሁሉም አጋር አካላት የዚህን ማዕከል ሁለንተናዊ የሥልጠና ዕድሎች በጋራ እንዲጠቀሙበት ወዳጃዊ ጥሪውን አቅርቧል።

​ተቋሙ በቀጣይም አገልግሎቱን በጥራትና በጥልቀት በማሳደግ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል።

📸ከበደ መክብብ

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2