ለደስታና ለጭፈራ የቡድን ጓደኞቹ ጋር አልሄደም፤ ፈንጠዚያን አላስቀደመም፤ ይልቁንስ ቀን ጎድሎበት በድንጋጤ ደርቆ ወደ ቆመው፥ በብርሃን መሃል በጨለማ ወደተዋጠው፥ ወደ ብሄራዊ ቡድን ተጣማሪው፥ ወደ ሀገሩ ልጅ ፈጥኖ ገሰገሰ፤ ከሁሉ ቀድሞ ደረሰና ለረጅም ደቂቃ አቅፎት አፅናናው፤ እንባውን አበሰለት፤ አይዞህ ወንድሜ አለው
የ32 አመቱ ብራዚላዊ የፒኤስጂ አምበል ማርከስ አኦስ ኮሪአ፥ ማርኪኒዮስ፥ ትናንት በሻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ በአለም ፊት ያሳየው ሰዋዊ እዝነት የሚሊዮኖችን ልብ ነክቷል
ከማርኪኒዮስ በአራት አመት የሚያንሰው የ28 አመቱ ገብርኤል ዶ ሳንቶስ ማጋሊሽ ክለቡ አርሴናል እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የእሱ ሚና ከፍተኛ ነበር፤ የቡድኑ ምሰሶ ሆኖ ሰንብቷል፤ ትናንት በጨዋታውም ሜዳ ላይ ከነበሩት የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች መካከል ብዙ ኳስ ያመከነው እሱ ነው፤ 13 ኳሶችን ተከላክሎ አውጥቷል፤ መጨረሻው ግን አላማረም፤ ቀን ጣለው፥ እድልና ድል ፊቱን አዞሩበት፤ እንደ ሮቤርቶ ባጂዮና ጆን ቴሪ፥ እንደ ዴቪድ ትሪዚጌና ቡካዮ ሳካ በታላቅ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ወሳኝ መለያ ምት ስቶ በህይወቱ ጥላ ሆኖ የሚከተለው አስቀያሚ ታሪክ አጋጠመው
በዚያች ቅፅበት አሸናፊዎቹ ፒኤስጂዎች ሜዳው አልበቃ ብሏቸው በደስታ ማዕበል ሲናጡ ከእነሱ ወገን የሆነው ማርኪኒዮስ ግን ተነጥሎ ወደ አርሴናሉ ተከላካይ ሄደ፤ እጁን አፉ ላይ ጭኖ በደመነፍስ የሚራመደው ገብርኤል ጋር ሲደርስ ማርኪኒዮስን ማንም አልቀደመውም፤ በስታዲየሙ ከሚሰማው የደስታ ጩኸት በላይ ጎልቶ በወጣ ልባዊ ፍቅር ምድር የዞረችበትን የሀገሩን ልጅ አፅናናው፤ እንደ ወንድሙ፥ እንደ ልጁ አጥብቆ ይዞ አበረታው፤ ልብ የሚነካ ነበር፤ የአርሴናሉ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድም ለማርኪኒዮስ ተግባር ያለውን ክብርና አድናቆት ከምስጋና ጋር አቅርቧል
ሁለቱ ብራዚላዊያን፥ ሁለቱ ሳኦፖሎ ተወልደው ያደጉ ተጫዋቾች፥ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ማርኪኒዮስና ገብርኤል እስካሁን በብሄራዊ ቡድን 16 ጨዋታዎችን በጋራ ተጣምረው ተጫውተዋል፤ በቀጣዩ የአለም ዋንጫም የተከላካይ ክፍሉን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል
የአራት ልጆች አባቱ ማርኪኒዮስ በርካታ ክብረወሰኖችን በስሙ አስመዝግቧል፤ በሁለት ተከታታይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜዎች በአምበልነት ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው ብራዚላዊ ሆኗል፤ በአውሮፓ መድረክ 122 ጨዋታዎችን የተጫወተ ቀዳሚው ብራዚላዊ ለመባልም በቅቷል፤ በ13 አመታት የፒኤስጂ ቆይታው ለክለቡ ብዙ ጨዋታ ያደረገ፣ 11 የሊጉን ዋንጫ ጨምሮ በጥቅሉ ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ያመጣና ሌሎች ስኬቶችን ያገኘ አምስት ቁጥር ለባሽ ደጀን ለመሆን በቅቷል
ትናንት ደግሞ በአምበልነቱ ዋንጫውን በአለም ፊት ከሁሉ ቀድሞ በከፍታ ከማንሳቱ በፊት ልዩ ሰብአዊ ምግባር ፈፅሞ በአለም ፊት ስሙን በክብር ከፍ አድርጓል፤ ማርኪኒዮስን መሳይ የሃገር ልጅ፥ እሱን መሳይ አርአያ ሰብ፥ ከደስታ መሀል ያዘነውን የሚፈልግ ፈጥኖ ደራሽና እንባ አባሽ በምድሪቷ ላይ ይብዛ!
(ታምሩ ዓለሙ)
Source: GetuTemesgen









No comments yet.