የዊ ሻምፒዮንስ ( We Champions 2026 )
የስፖርት ፌስቲቫል እየተሰናዳ ነው
#Ethiopia | የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ከ22 ዓመታት ረጅም የጥበቃ ጊዜ በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማሸነፉን አስመልክቶ፣ ይህንን ታሪካዊ ድል ለማክበር የተሰናዳውና በሀገራችን የመጀመሪያው ግዙፍ የስፖርት መድረክ የሆነው የዊ ሻምፒዮንስ 2026 ( We Champions 2026 ) የእግር ኳስ ፌስቲቫል በመጪው ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በታላቅ ድምቀት እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በጎርደን ኢንተርቴይመንት አዘጋጅነት ለሚቀርበው ለዚህ ትልቅ ሁነት አዋሽ ባንክ በአፕክስ ኖብል ፕሮግራሙ አማካኝነት ዋነኛ ስፖንሰር በመሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ልዩ መርሃ ግብር የስፖርቱን ፍቅር፣ ታማኝነትን፣ ባህልን፣ መዝናኛንና ስፖርታዊ እሴቶችን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ከ30 ሺህ በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን፣ የዓለም አቀፍ ስፖርት ተዋናዮችንና እውቅ ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ ላይ የሚሰበስብ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው የደስታ መግለጫ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዝግጅቱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በበለጠ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የስፖርት መገናኛ ብዙኃንንና የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን ትኩረት በመሳብ የሀገሪቱን የቱሪዝም ፍሰት፣ የባህል ገጽታ እንዲሁም ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን የማስተናገድ ብቃት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ታምኖበታል።
በዕለቱ ከሚታደሙት የክብር እንግዶች መካከል የቀድሞው የአርሰናልና የቱኒዥያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ራዲ ጃይዲ የሚገኝበት ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደራሽነትና ተፅዕኖ ካላቸው የእግር ኳስ ሚዲያ አንዱ የሆነው የኤኤፍቲቪ መስራቾችና ተወካዮችም በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ መረጋገጡን በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።
ወደ ስታዲየም ለመግባት የሚያስችሉ የትኬት ሽያጮችን አስመልክቶ አዘጋጆቹ በሰጡት ማብራሪያ፣ መግቢያ ትኬቶችን ማግኘት የሚቻለው በአዋሽ ባንክ የአፕክስ ኖብል ፕሮግራም በኩል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
የመዝናኛ ክፍሉን ይበልጥ ማራኪና ድምቅ ለማድረግ ከአስር በላይ ታዋቂና ወጣት የሙዚቃ አርቲስቶች የተጋበዙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ታደለ ሮባ፣ ልጅ ሚካኤል (ፋፍ)፣ ሳሚ ዳን፣ አስማማው እሸቱ፣ ራሄል ጌቱ፣ ሮማን ማይክ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሚካ ያኖ፣ አማኑኤል የማነ፣ አዲስ ሙላት፣ እዩ ፀጋ እና ኩሉ ሱሌ ይገኙበታል።
የአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 6:00 ሰዓት ጀምሮ ለታዳሚዎች ክፍት የሚሆን በመሆኑ፣ ተመልካቾች በጊዜ በመገኘት ቦታቸውን እንዲይዙ አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
#WeChampions2026 #Arsenal #AwashBank #ApexNoble #GordonEntertainment #AFTV #RadhiJaidi #FootballFestival #EthiopianTourism #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.