#FastMereja I በኦሮሚያ ክልል ወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሥራቸው ላይ በነበሩት ክብርት ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ ላይ የተፈጸመው የጦር መሣሪያ ጥቃት በሕግ የበላይነትና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የተቃጣ ከባድ ጥቃት መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። ፍርድ ቤቱ ጥቃቱን በጽኑ በማውገዝ፣ ጥፋተኞች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡና ለዳኞች ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው ይፋዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ክብርት ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ የዳኝነት ሥራቸውን በሕግና በሙያ ሥነ-ምግባር መሠረት በማከናወን ላይ እያሉ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በባለጉዳይ በተፈጸመ የጦር መሣሪያ ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል። ድርጊቱ በአንድ ዳኛ ላይ ብቻ የተፈጸመ ወንጀል ሳይሆን፣ በዳኝነት ነፃነትና በሕግ የበላይነት ላይ የተቃጣ ከባድ ጥቃት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
እንዲህ ያሉ በፍትሕ ሥርዓቱ ተዋናዮች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች የሕግ የበላይነትን ለማዳከም የሚደረጉ ተግባራት መሆናቸውን የጠቀሰው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት በፍጥነት፣ በተሟላ እና በግልጽ ሁኔታ ተጣርቶ ተጠያቂዎች በአስቸኳይ በሕግ ፊት እንዲቆሙ ጠይቋል።
በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዳኞች እና የፍትሕ ዘርፍ ባለሙያዎች ደህንነት እንዲጠናከርና ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይደገሙ አስፈላጊው የጥበቃ እርምጃ እንዲወሰድ ያሳሰበው ፍርድ ቤቱ፣ ለሟች ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ ቤተሰቦች፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላው የፍትሕ ማኅበረሰብ ጥልቅ ሐዘኑን በመግለጽ መጽናናትን ተመኝቷል።
Source: FastMereja







No comments yet.