ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የተፈጥሮ ፀረ ተባይ ነፍሳት ማራቢያ ማዕከል በይፋ አስመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በአለም አቀፍ የአበባ ንግድ ዘርፍ ታዋቂ በሆነው ዱመን ኦሬንጅ ስር የሚንቀሳቀሰው ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ጠቃሚ ነፍሳትን የሚያረባ ዘመናዊ ማዕከል በቆቃ ነገዎ በሚገኘው የእርሻ ቦታው ስራ አስጀምሯል።

ይህ አዲስ መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ያለ ኬሚካል ሰብሎችን በተፈጥሯዊ መንገድ በመንከባከብ ዘላቂ ግብርናን ማስፋፋት እንደሚቻል ያሳየ ትልቅ እመርታ ነው።

ማዕከሉ በዋናነት በማስዋቢያ ዕፅዋትና አበቦች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮችን ተለቅመው እንዲጠፉ የሚያደርጉ ስዊርስኪ እና ካሊፎሚከስ የተባሉ ጠቃሚ ትሎችን ያመርታል።

ይህም ሰው ሰራሽ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን በከፍተኛ ደረጃ በማስቀረት በተፈጥሯዊ መንገድ ተባይን የመቆጣጠር ዘዴን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ያስችላል።

የዚህ የቴክኖሎጂ ውጤት ጥቅሞች ዘርፈ ብዙ ሲሆኑ በኬሚካል ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ የሰራተኞችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ጤና ይጠብቃል።

በተጨማሪም ወደ ውጭ በሚላኩ የአበባ ምርቶች ላይ የሚኖረውን የኬሚካል ቅሪት ስጋት በማስቀረት የሀገሪቱን ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተመራጭ ያደርገዋል።

ጠቃሚ ነፍሳቱን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከመታደጉም በላይ በአየር ትራንስፖርት ጭነት ሳቢያ የሚፈጠረውን የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀትን በእጅጉ ይቀንሳል።

ይህ ማዕከል በዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጠቃሚ ነፍሳትን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ይህም በ40 ሄክታር መሬት ላይ ለሚለማው እርሻ በቂ የተፈጥሮ መከላከያ ለማቅረብ ያስችላል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዮርዳኖስ ጀማል ሽኩሪ እንደገለጹት ይህ ማዕከል ተፈጥሮን በጥበብ በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ማሳያ ሲሆን ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮችም ይህንን ፈር ቀዳጅ አሰራር እንዲከተሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በኦሮሚያ ክልል እአአ በ2003 የተቋቋመው ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እስከ 100 ሄክታር መሬት ላይ በመንቀሳቀስ በዓመት ከ120 ሚሊዮን በላይ የተቆረጡ አበቦችና አፅቆችን ለውጭ ገበያ ያቀርባል።

ተቋሙ ለአካባቢው ነዋሪዎች እስከ 2500 የሚደርስ የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 72 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው። ከዚህ ባለፈም በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በጤና አገልግሎት እና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ዙሪያ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ እየተወጣ ይገኛል።

ይህ የቆቃ ነገዎ የነፍሳት ማራቢያ ማዕከል በምስራቅ አፍሪካ ከኬንያና ታንዛኒያ በመቀጠል ሶስተኛው ቢሆንም በይዘቱና በዘመናዊነቱ ግን ኢትዮጵያን በቀጠናው ቀዳሚ ያደርጋታል።

#Horticulture #Agriculture #Environment #Sustainability #EcoFriendly #RedFoxEthiopia #DumenOrange
#getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2