ከአቅም በላይ የሆነው የትራንስፖርት ዋጋ

- Advertisement -
Sidebar AD

አብዛኛው የመንግሥትም ሆነ የግል ሠራተኞች ነጋዴዎችም ሆኑ የቀን ሠራተኞች የዕለት ሥራቸውን የሚጀምሩትና የሚያጠናቅቁት በትራንስፖርት ነው። ይሁን እንጂ በየወቅቱ የሚወጡት አዳዲስ የታሪፍ ማሻሻያዎች በትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ላይ ተገማች ያልሆነ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናጋትን ተገን በማድረግ በአገር ውስጥ የሚደረጉ የዋጋ ማስተካከያዎች፣ ዛሬ ላይ የዜጎችን የመንቀሳቀስና የኢኮኖሚ አቅም በእጅጉ እየፈተኑት ነው፡፡ ታሪፍ በየወቅቱ ይጨምራል፣ የተሳፋሪው ደመወዝና ገቢ ግን ባለበት እንደቀጠለ ነው፡፡

አቶ መለስ አምሳሉ ከሸገር ከተማ ኮዬ ፈጨ ተነስተው ሽሮ ሜዳ በየዕለቱ ከባለቤታቸው ጋር ለሥራ ይመላለሳሉ፡፡ ‹‹አጋጣሚ የእኔም የባለቤቴም ሥራ አንድ አካባቢ በመሆኑ ሁሌም በጧት ተነስተን ተያይዘን ነው የምንወጣው›› የሚሉት አቶ መለሰ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ በከተማ ባስ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በታክሲ እየተመላለሰን ነው የምንሠራው፡፡ እኔም ባለቤቴም አብረን ስለምንሄድ ነው መሰል የትራንስፖርቱ ክፍያ ከሁሉም በላይ ያሰለቻል የሚዘለቅ አይመስልም›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በቀን ከባለቤታቸው ጋር ከ300 እስከ 500 ብር ለትራንስፖርት እንደሚያወጡ የተናገሩት አቶ መለስ፣ የሚከፈላቸው ደመወዝና የሚያወጡት የቀን ወጪ ሊጣጣም እንዳልቻለ ይጠቁማሉ፡፡

በተለይ የትራንስፖርት ወጪው፣ ነዳጅ በጨመረ ቁጥርትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ዋጋ መጨመር በየቀኑ የተለያየ ክፍያ መጠየቅና ተደራድሮ መጫን፣ መሸት ካለ በእጥፍ እስከመጨመር መድረስ ለሕዝቡ ሸክም መሆኑን ይጠቁሟሉ፡፡

መንግሥት አምስት ብር ወይም አሥር ብር ታሪፍ ጨመረ ሲባል እነሱ ከተባለው እጥፍ በላይ አድርገው ይጨምራሉ፣ ኅብረተሰቡ ተመጣጣኝ ክፍያን ያስከፍሉ የነበሩት የከተማ አውቶብሶች ዛሬ ላይ በተደረገ ጭማሪ ውድ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹በምግብ፣ በዕቃና በሌሎች ነገሮች ላይ የሚደረገውን የዋጋ ጭማሪ አንዳንዱን ልታልፈው ትችላለህ፡፡ አንዳንዱም ለጊዜው ላያስፈልግ ስለሚችል ልተወው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ትራንስፖርት ልተው ወይም ለነገ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ከሥራህ ታክሲ አጣሁ ወይም ብር የለኝም ብለህ ብትቀርከደመወዝህ ይቀነሳል፤›› ሲሉም ያሉበትን ፈተና ይገልጻሉ፡፡

በተደጋጋሚ ከሥራ መቅረት እስከ መባረር ለሚያደርስ ቅጣት ይደረጋል በመሆኑም ትራንስፖርት ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡም ቢሆን ችግር አለበት›› የሚሉት አቶ መለስ፣ ‹‹አንዳንድ ተቆጣጣሪዎች በተለይ መነሻው ላይ ስንት ብርእንደተጠየቅን ሲጠይቁን፣ ትክክለኛውን አንናገርም፡፡ በመሆኑም ይኼ ነገር ለመንግሥት ቁጥጥርም አስቸጋሪ ይመስለኛል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የትራንስፖርት እጥረትና እጥረቱን ተከትሎ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በጣም እንዳስመረራቸው የሚናገሩት ደግሞ ወ/ሮ መሠረት ኃይሉ ናቸው፡፡

ወ/ሮ መሠረት ከአራብሳ ተነስተው መስቀል አደባባይአካባቢ ወደሚገኘው የሥራ ቦታቸው ዘወትር ይመላለሳሉ ‹‹አሁን ላይ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ችግሩ ተደራራቢ መሆኑ ነው፣ የመጀመሪያው ረዥም ሠልፍ መሠለፍ፣ ከዚያም ከታሪፍ በላይ መክፈል፣ ታሪፍ ነው ብለን ለመከራከር ስንሞክር ነዳጅ ስለጨመረ ጨምሯል እንባላለን፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ቤት እንዳልውል ከቤት ኪራይ ጀምሮ ያለው ወጪ ከአቅም በላይ ነው፡፡ ተሯሩጦ ለመሥራት ደግሞ ከሁሉም በላይየትራንስፖርት ወጪው ያሰለቻል፣ ነገር ግን ቁጭ ከማለት ይሻላል በሚል እየለፋን ለቤት ኪራይና ለትራንስፖርት እንሰጣለን፣ ለነገ ብንታመም፣ ብንሞት ብለን የምናስቀምጠው ጥሪት የለንም፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

እነዚህና መሰል ቅሬታዎች በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት መቀስቀስ ጋር ተያይዞ በነዳጅ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከተደረገ ወዲህ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ ጦርነት ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ከደረሰባቸው ሴክተሮች መካከልም የትራንስፖርት ዘርፉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡

በነዳጅ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ዞረው ዞረው ማረፊያቸው እንደ አቶ መለስና እንደ ወ/ሮ መሠረት ባሉ ተጠቃሚዎች ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር መንግሥት የትራንስፖርት ‹‹የታሪፍ ማሻሻያ በሚል በየወቅቱ ይጨምራል፡፡ መንግሥት ከሚጨምረው የታሪፍ ጭማሪ ባሻገር ጭማሪውን ተከትለው የሚጨምሩ አሽከርካሪዎች መበራከታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ የኅብረተሰቡን ገቢ ያላገናዘበ መሆኑን ተሳፋሪዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹በሁለት ዓመትና በሦስት ዓመት ምንም ዓይነት የደመወዝ ጭማሪ ሳይደረግልኝ በትራንስፖርት ታሪፉ ላይ ግን በቀላሉ ከሦስት ጊዜ በላይ የታሪፍ ጭማሪ በሚል ቢያንስ ከ2ዐ እስከ 3ዐ ብር በቀን በአንድ ጉዞ ላይ ጭማሪ መደረጉን አውቃለሁ፤›› ሲሉ የተናገሩት የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ አባት ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አዘውትረው የሚጠቀሙት የከተማ አውቶብስን ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ገቢያቸው ዝቅተኛ በመሆኑ በታክሲ መሄድ ስለማይችሉ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የባስ አገልግሎት ታሪፉም ቢሆን የሚቀመስ አልሆነም ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን ኅብረተሰቡ መንግሥት ካስቀመጠው ታሪፍ በላይ የሚገደድባቸው ሁኔታዎች፣ በተለይ በምሽት ቢኖሩም፣ ተገቢው ቁጥጥር አለ ብለው እንደማያምኑም ያክላሉ፡፡

የሚኒባስ አሽከርካሪው ተስፋ ብርሃኑ፣ ተሳፋሪዎች የሚያቀርቡት ጥያቄም ሆነ አስተያየት ትክክል ነው፣ ነገር ግን ያላወቁልን ነገር ቢኖር የእኛን መቸገር ነው ሲል ተናግሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት ነዳጅ ከማደያ እስከ 18ዐ ብር ነው እየከፈልን የምንቀዳው፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ሲጨምር እኛ ታሪፍ አንጨምርም፡፡ ሰው በየዕለቱ ከቤት ወደ ሥራ ቦታ ከሥራ ቦታ ወደ ቤት ሲመላለስ 5ዐ ሆነ መቶ ሲያወጣ ከባድ ይሆንበታል፡፡

እኛ ደግሞ ከነዳጅ ባሻገር የምናወጣው የጥገና ወጪ እንዲሁ የሚነገር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ የተለያዩ ሕጋዊ የሆነም ሕጋዊ ያልሆነም ምክንያቶችን በመፍጠር በየመንገዱ ለቅጣት የምናወጣው ወጪም ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡

እንደ አሽከርካሪው፣ አብዛኛው ሹፌር የሚሠራው በልቶ ለማደር ነው፡፡ ከሰዓት እላፊ በላይ ከሠራ ምን አልባት ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ አብዛኛው ሰው ዘይትና ሽንኩርት መጨመሩን ያውቃል፡፡ ነገር ግን ትራንስፖርት ከአምስት ወር በፊት በነበረው የሚቀጥል የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ብዙ ሰዎች የትራንስፖርት ማሻሻያ ተደርጓል መባሉን የሚሰሙት ቆይተው ነው፡፡

እነዚህን መሰል ከኅብረተሰቡና ከአሽከርካሪዎች የተነሱ ጥያቄዎችን በተለይ የነዳጅ አቅርቦት ተስተካክሏል ከተባለ ወዲህ ያሉ መሻሻሎች ካሉ ምላሽና ማብራሪያዎችን ለማግኘት ጉዳዩ ወደሚመለከተው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ሐሙስ ግንቦት 2ዐ ቀን 2018 ዓ.ም. ከሰዓት በቢሮው ብንገኝም፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስለሚበዙ በወቅቱ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ በቃል አሳውቀውናል፡፡

ዘገባው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1