#FastMereja I በትግራይ ክልል ያለውን የጦርነት ሥጋት በመሸሽ በርካታ ወጣቶች ክልሉን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የክልሉ ወጣቶች እና በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች እንደሚሉት ማህበረሰቡ ተደጋግሞ በሚመጣው ጦርነት መሰላቸቱን ይናገራሉ።
በትግራይ እየተካሄደ ባለው የጦርነት ዝግጅት ምክንያት አጠቃላይ ማህበረሰቡም ሆነ ወጣቱ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል ሲል አስተያየቱን ለዶይቼ ቬለ ያጋራው አንድ የመቐለ ነዋሪ ወጣት፤ “በተለይም ሺራሮ አከባቢ ከሰሞኑ የተወሰደው የድሮን ጥቃት እርምጃ ድንጋጤን ፈጥሯል” የሚለው ወጣቱ ከዚሁ የተነሳ አሁን ላይ በርካታ ወጣት ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎችም መሃል አገር አከባቢ በመሸሽ በተጨማሪ ጦርነት ላለመሳተፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል ነው ያለው፡፡ “በክልሉ በተለይም ከመቀሌ ውጪ ባሉ አከባቢዎች ላይ ወጣቱ ወደ አስገዳጅ የጦርነት ምልመላ እየገባ ነው” የሚለው ወጣቱ ከዚሁ የተነሳ የተቻለው ወጣት በሙሉ ትግራይ ለቆ ለመውጣት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ሌላው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣትም ባከለው ተመሳሳይ አስተያየቱ፤ “ወጣቱ አሁን መማር መስራት እንጂ ወደ ጦርነት መግባት አይፈልግም” በማለት እሱ ራሱን ጨምሮ በርካታ ወጣት “የማይከፈለው ዋጋ እየከፈለ ከክልሉ እየሸሸ እየወጣ” መሆኑን ገልጿል፡፡ ወጣቱ እራሱም ከክልሉ ለመውጣት የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጦ እየተጠባበቀ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
በትግራይ ክልል እንደ ከዚህ ቀደሙ ደም አፋሳሹ ጦርነት ወጣቶች ወደ ግጭት ከመግባት ይልቅ የጦርነት ሃሳቡን የማይገዙት ለምን ይሆን ተብለው የተጠየቁት ወጣቶቹ፤ “በቂ ምክንያት የለንም” ይላሉ፡፡ “ትናንት ከደፈረን ሃይል ጋር መስራት አልፈልግም” ሲል አስተያየቱን ሰጠው አንደኛው ወጣት፤ ወጣቱ በዚህ የሚቀየር የለም የሚለውን ሃሳብ በመያዝ ከጦርነቱ መሸሽን ምርጫው ማድረጉን ነው ያመለከተው፡፡ ሌላኛውም አስተያየቱን ያከለው የመቀሌ ከተማ ነዋሪው ወጣት፤ “ወጣቱ ካለፈው ጦርነት በመማር አሁን ሰላም ወዳለበት ሄዶ ሰርቶ መለወጥ ነው ፍላጎቱ” ሲል ሃሳቡን አጋርቷል፡፡
በትግራይ የጦርነት አይቀሬነት አሁን አሁን ጎልቶ እየመጣ መሆኑን በማስረዳት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴዎች በቅርበት የሚከታተሉት ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ እንደሚሉት አሁን አሁን አጠቃላይ እንደማህበረሰብም ሆነ ወጣቱ ክፍል በትግራይ ባለው የፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ተስፋ እየቆረጠ መጥቷል ነው የሚሉት፡፡ “በተለይም ከፕሪቶሪያው የቅጭት ማቆም ስምምነቱ በኋላ የትግራይ ፖለቲካ ተከፋፍሎ ታይቷል” ያሉን ፖለቲከኛው፤ በተለይም ወጣቱ ሃይል ተጨማሪ ዋጋ የመክፈል ፍላጎትን ፈጽሞ እያሳየም አይደለም ነው ያሉት፡፡ በመሆኑ አቅም ያላቸው ወጣቶችም ሆኑ ሌሎችም እየተጋገዙ ከክልሉ በመውጣት ሌሎች አከባቢዎች ላይ ሄደው ስራ ፈጥረው ህይወታቸውን የመምራት አዝማሚያዎችን እያሳዩ ስለመምጣታቸውም በሰፊው እየተስተዋለ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ዘገባው የዶይቼ ቬለ ነው!
Source: FastMereja









No comments yet.