#Ethiopia | የሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት ዛሬ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡
አዋጁ የጸደቀው በሁለት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ ነው፡፡
“ማጓጓዣው የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ የተገኘ ከሆነ የተሽከርካሪው ባለቤት የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያወጣው መመሪያ በሚወስነው መሰረት እንደነገሩ ክብደት እንዲሁም እንደጭነቱ መጠን በገንዘብ መቀጮ ወይም ማጓጓዣውን እስከመውረስ ሊያደርስ በሚችል ቅጣት ሊቀጣ ይችላል”ይላል ዛሬ የጸደቀው አዋጅ ፡፡
አዋጁ እቃዎችን ለመደበቅ የሚያስችል አካል የተገጠመለት ተሽከርካሪ እና ሙሉ በሙሉ የኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ ሲጓጓዝ የተገኘ ተሽከርካሪ እንዲወረስ ደንግጓል፡፡
አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ ኮንትሮባንድ የጫኑ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የሚቀጡት የብር መጠን 100,000 ነበር ፡፡
ይህ የገንዘብ ቅጣት ዝቅተኛ ስለሆነ ችግርን ከመቀነስ ይልቅ ኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲባባስ ማድረጉን በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡
በተሸሻለው አዋጅ ግን መኪናው ወይንም ተሸከርካሪው ኮንቶሮባንድ ጭኖ ከተያዘ ሙሉ በሙሉ እንዲወረስ ያዛል ፡፡
በዙህም መሰረት ዕቃዎቹን ለመደበቅ እንዲያስችል ሆኖ የተሠራ፣ የተለወጠ ወይም መደበቂያ አካል የተገጠመለት ከሆነ ፣ማጓጓዣው የጫነው ዕቃ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ በሚወስነው መጠን የኮንትሮባንድ ዕቃ የሆነ እንደሆነ የዕቃው ግምታዊ ዋጋ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ማጓጓዣው ተወርሶ ለመንግስት ገቢ ይደረጋል ይላል፡፡
በተጨማሪም ማጓጓዣው ከመወረሱ በፊት የማጓጓዣው ባለቤት ይህንኑ እንዲያውቀው ሊደረግ እና ማጓጓዣው ጥቅም ላይ ስለዋለበት ሁኔታ ማስረጃ እንዲያቀርብ እድል ሊሰጠው ይገባል ሲል ያክላል።
ይህም የኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቀረት እና የዘርፉ ተሳታፊዎች ለመቀነስ እንደሚረዳ ተነግሯል፡፡
ማሻሻያ አዋጁ አስተዳደራዊ መቀጫዎች በተመለከተ ደግሞ የተጣለባቸውን ግዴታ ያልተወጡ አጓጓዦች፤ በኮንትሮባንድ ንግድ ተሳታፊ የሆኑ የማጓጓዣ ባለቤቶች፤ የጉምሩክ ህግን የተላለፈ የመጋዘን ባለፈቃድ፤ በጌዜያዊነት ወደ አገር ያስገባውን እቃ የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ያላስወጣ ሰው የሚኖርባቸው አስተዳደራዊ ቅጣት በአዋጁ ከፍ እንዲል ተደርጎ ተሻሽሏል።
ይግባኝ ለማቀረብ የሚከፈል ቀረጥ እና ታክስ አስመልክቶ አስመጪው ያመነውን ቀረጥ እና ታክስ ከፍሎ እና ልከፍል አይገባም የሚለውን ቀረጥ እና ታክስ 50 በመቶ አስይዞ ይግባኝ ማቀረብ እንዲችል ተሸሽሏል፡፡
በስራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ግን በጉምሩክ ኮሚሽን እንዲከፍል በተጠየቀው ቀረጥ እና ታክስ ያልተስማማ አስመጪ ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኝ ሊያቀርብ የሚችለው ቀረጥ እና ታክሱን ሙሉ በሙሉ ከከፈለ በኋላ እንድሆነ ይታወቃል፡፡
ይህ ድንጋጌ ሀገ-መንግስቱ ለዚጎች የተሰጠውን አቤቱታ የማቅረብ መብት የሚገድብ በመሆኑ ተሸሽሏል ይላል አዋጁ፡፡
ማሻሻያው ስለ አጓጓዥ ግዴታዎች እና ኮንትሮባንድ በማጓጓዝ ድርጊት ስለ መሳተፍ በተመለከተ ማንኛውም አጓጓዥ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ የመንገደኞች ወይም የጭነት መግለጫ ካላቀረበ፣ ከተፈቀደለት ሰው በስተቀር ሌላ ሰው ወደ ማጓጓዣው እንዲገባ ካደረገ ወይም ማጓጓዣው ከጉምሩክ ወደብ እንዲወጣ ከተወሰነ በኋላ ምክንያቱን ለጉምሩክ ሹም ሳያስረዳና ፈቃድ ሳያገኝ እንዲቆይ ካደረገ፤ ከ4,000 ብር ባላነሰ እና ከ10,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል ይላል፡፡
በማከልም ማንኛውም አጓጓዥ የጉምሩክ ወደብ በደረሰ ማጓጓዣ ላይ የጉምሩክ ሹም በሌለበት ዕቃ የጫነ፣ ያራገፈ ወይም ለመጫን ወይም ለማራገፍ ሙከራ ያደረገ እንደሆነ ከብር 15,000 በማያንስና ከብር 20,000 በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ደንግጓል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ የተገኘው ማጓጓዣ ባለቤት በኮንትሮባንድ ወንጀል ተሳታፊ ሆኖ ከተገኘ የሚኖርበት የወንጀል ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ወንጀሉ እንዳይፈጸም ለማድረግ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ ካልወሰደ የኮንትሮባንድ እቃው መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ የተጫነውን የኮንትሮባድ ዕቃ ዋጋ አንድ መቶ ፐርሰንት ወይም ብር 200‚000 ከሁለቱ አነስተኛውን የገንዘብ መቀጫ ይቀጣል፡፡
የጭነት ማሸጊያን ወይም ኮንቴነርን በመክፈት የኮንትሮባንድ ዕቃን ቀላቅሎ ጭኖ የተገኘ ማጓጓዣ ባለቤት ዕቃው መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ የማጓጓዣው ባለቤት ብር 500,000 የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
ዘገባው የሸገር ሬዲዮ ነው።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.