በዓለም ዋንጫ ላይ እንዲዳኝ ተመርጦ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለው ሶማሊያዊው እውቅ የኢንተርናሽናል እግር ኳስ ዳኛ ዑመር አርታን ወደ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ሲመለስ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ የጀግና አቀባበል ተደረገለት።
የአፍሪካ ምርጥ ዳኞች ተርታ የሚመደበውና እ.ኤ.አ በ2025 የአህጉሪቱ ምርጥ ወንድ ዳኛ ተብሎ የተመረጠው ዑመር አርታን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ በመዳኘት የመጀመሪያው ሶማሊያዊ በመሆን ታሪክ ሊሰራ ተዘጋጅቶ ነበር።
ዳኛው ባለፈው ሳምንት በኬንያ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ህጋዊ ቪዛ የተሰጠው ቢሆንም ቅዳሜ እለት ሚያሚ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ግን በአሜሪካ የድንበርና የጉምሩክ ጥበቃ አካል “በደህንነት ማጣራት ስጋት” (Vetting concerns) ምክንያት መግቢያ ተከልክሏል።
አሜሪካ ውሳኔውን ተከትሎ ዝርዝር መረጃ ካለመስጠቷም በላይ የአንደኛዋ አስተናጋጅ ሀገር ክልከላን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (FIFA) ዳኛውን ከዓለም ዋንጫው የዳኞች ዝርዝር ውስጥ ለመሰረዝ ተገድዷል።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ የፊፋ ዕውቅና ያለውን ከፍተኛ ዳኛ ወደ ሀገር እንዳይገባ መከልከሏ በዓለም ዙሪያ ባሉ የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ውሳኔው አሜሪካ እንዲህ ያሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ብቃት አላት ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳባት አድርጓል። ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት በትራምፕ አስተዳደር የስደተኞች ቁጥጥር ፖሊሲ ምክንያት አዲስ የጉዞ ገደብ ከተጣለባቸው 40 ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ለዚህ ክልከላ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።
ዳኛ ዑመር አርታን ዛሬ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት 3:30 በሞቃዲሾ አደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የስፖርት ቤተሰቦች የሶማሊያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ለሰዓታት ሲጠባበቁት ቆይተዋል።
አውሮፕላኑ ሲያርፍም ደጋፊዎቹ በሶማሊያ ባንዲራ ያለበሱት ሲሆን፣ በፖሊስ ታጅቦ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የቪአይፒ (VIP) ማረፊያ አምርቷል። እዚያም በሶማሊያ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር እና በሶማሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል።
ዳኛው ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ለተደረገለት ድጋፍ የሶማሊያን መንግስት፣ ህዝብ እና ፊፋን አመስግኗል። “እግዚአብሔር ከፈቀደ በሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ላይ እንደምገኝ ቃል እገባላችኋለሁ፤ የሶማሊያ ህዝብ በዚህ እንዲረጋጋና በራሱ እንዲተማመን እፈልጋለሁ” ብሏል።
አክሎም “የሶማሊያን ስም የመጠበቅ ኃላፊነት የሁላችንም ነው። ሀገራችን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ብትሆን የእኛ ናት ያ ባንዲራና ፓስፖርትም የእኛ ነው በማለት ለወጣቱ መልዕክት አስተላልፏል።
ለዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነትና በአሸባሪው አልሸባብ ምክንያት የወጣቶቿ ተስፋ በተገደበባት ሶማሊያ የዑመር አርታን መከልከል ለብዙዎች የልብ ስብራት ቢሆንም፣ ሕልምን ተከትሎ መጓዝ ምን ያህል ትልቅ ደረጃ እንደሚያደርስ ግን ማሳያ ሆኗል።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር (X) ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የደረስክበት የታሪክ ምዕራፍ ምንም ቢሆን አይቀየርም። በሙያህ ጥግ ላይ በመድረስህ ብቻ በትውልድ ሀገርህ ላለው አዲስ ትውልድ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥረሃል በለፋህበትና በገባህበት የሜዳ ሳር ላይ እንዳትቆም መደረግህ ይህንን የታሪክ እውነት አይለውጠውም በማለት ለዳኛው ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።

Source: Yeneta Tube









No comments yet.