አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ እና አትሌት ዘመናይ አያና የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት መፈፀማቸው በመረጋገጡ ቅጣት ተጣለባቸው።

- Advertisement -
Sidebar AD

አትሌት ጉዳፍ ፀጋየ እና አትሌት ዘመናይ አያና ቀደም ሲል በተደረጉ የአበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ምርመራዎች የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግ በመጠቀም ተጠርጥረው ጉዳያቸው ሲጣራ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት የአለም አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት(AIU) እ.ኤ.አ ዲሴምበር 05 ቀን 2025 ዓ.ም ከውድድር ጊዜ ውጭ ባካሄደው ምርመራ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ ‘ሌትሮዞል’ (Letrozole) የተባለውንና በማንኛውም ጊዜ እንዳይሰድ የተከለከለውን መድኃኒት ተጠቅማ መገኘቷ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለፉት ጊዜያት ጉዳዩ ሲታይ የቆየ ሲሆን የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) እና የአለም አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት (AIU) ከአትሌቷ ጋር በተፈጠረ የጋራ ስምምነት (Case Resolution Agreement) በአትሌቷ ላይ እ.ኤ.አ ከሰኔ 01/2026 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2026 ዓ.ም የአራት (4) ወር እገዳ (Period of Ineligibility) ቅጣት ተጥሏል፡፡ በተጨማሪም አትሌቷ እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 5/2025 ዓ.ም ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው የውድድር ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ፣ ሜዳሊያዎች እና የገንዘብና ሌሎችም ሽልማቶች እንዲመለሱ ተወስኗል። የህግ ጥሰቱ የተፈፀመው ከአትሌቷ ጤንነት ጋር በተያያዘ በተሰጠ የህክምና ፈቃድ አገልግሎት (Therapeutic Use Exemption) እንደሆነ የተመላከተ ሲሆን የተሰጠው ውሳኔም ይግባኝ የማይቀርብበትና የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑ ታውቋል።

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን (ETH-ADA) በአትሌት ዘመናይ አያና ላይ እ.ኤ.አ
ግንቦት 4/2025 ዓ.ም ከውድድር ጊዜ ውጪ ባካሄደው የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ አትሌቷ ‘የአናቦሊክ አንድሮጄኒክ ስቴሮይድ’ (Testosterone) ንጥረ ነገር ተጠቅማ መገኘቷ ታውቋል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ባለፉት ጊዜያት በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን አትሌቷ ጥፋተኛ መሆኗ በመረጋገጡ ጊዜያዊ እገዳ ከተጣለበት እ.ኤ.አ ከጥር 21/2026 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 22/2030 ዓ.ም ድረስ ለአራት (4) ዓመታት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ (Period of Ineligibility) ተጥሎባታል፡፡ በተጨማሪም አትሌት ዘመናይ ምርመራ ከተደረገበት እ.ኤ.አ ከግንቦት 4/2025 ዓ.ም ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው ማንኛውም የውድድር ውጤቶች፣ ሜዳሊያዎች እና የገንዘብ ሽልማቶች በሙሉ እንዲሰረዙና ተመላሽ እንዲሆኑ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን (ETH-ADA) አትሌቶችም ይሁን ሌላ ማንኛውም አካል የስፖርቱን ደህንነትና የአገርን ገጽታ ከሚያበላሹ መሰል የአበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ወንጀሎች እንዲታቀቡና የግል ኃላፊነት (Strict Liability) መርህን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በድጋሚ ያሳስባል። በየደረጃው የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥርም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን !!!


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1