#Ethiopia | ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት የረጅም ርቀት ሯጭ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት እና በኋላ በተደረገላት የዶፒንግ ምርመራ የተከለከለ ንጥረ ነገር በመገኘቱ ምክንያት የአራት ወራት እገዳ ተጥሎባታል።
የ29 ዓመቷ ስመ ጥር አትሌት የገጠማትን የጤና እክል ለማከም የተጠቀመችው መድኃኒት በዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ ዋዳ የተከለከሉ ዝርዝር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህንኑ ጉዳይ አትሌቷ ማመኗ ተገልጿል።
ጉዳፍ በአውሮፓውያኑ 2020 በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን በ2022 በ5ሺህ ሜትር እንዲሁም በ2023 በ10ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፏ ይታወሳል።
በባለሙያዎች እንደተብራራው በአትሌቷ የሰውነት ናሙና ውስጥ የተገኘው ይህ መድኃኒት በሰውነት ውስጥ ያለውን የኢስትሮጅን መጠን ለመቀነስና የጡት ካንሰርን ለማከም የሚያገለግል ነው።
ጉዳፍ ፀጋይ በጥር ወር መጨረሻ ላይ የምርመራው ውጤት ከደረሳት ማግስት ጀምሮ የጤና እክሏን ለማከም መድኃኒቱ በሀኪም እንደታዘዘላት የሚያሳዩ ደጋፊ የሕክምና ሰነዶችንና ማስረጃዎችን አቅርባለች።
በየካቲት ወር ላይም መድኃኒቱን በሕክምና ምክንያት እንድትጠቀም ልዩ ፈቃድ እንዲሰጣት ለዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥያቄ አቅርባ የነበረ ቢሆንም የሕክምናው ሂደት መስፈርቱን እንደሚያሟላ ቢረጋገጥም ቅጣቱን ወደኋላ መልሶ ለማንሳት የቀረበው ጥያቄ ግን ውድቅ ሆኗል።
የአትሌቲክስ ስፖርትን ንጽህና እና ተአማኒነት የሚቆጣጠረው ኤአይዩ ባወጣው መግለጫ አትሌቷ ሆን ብላ የፈጸመችው ጥፋት ወይም ቸልተኝነት አለመኖሩን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ አትሌቷ ጥፋቱን ወዲያውኑ አምኖ መቀበሏ እና አስቀድማ ብታሳውቅ ኖሮ ፈቃዱ ሊሰጣት የሚችልበት ዕድል እንደነበር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጣለባት የአራት ወራት እገዳ ተገቢ መሆኑን ተቆጣጣሪው አካል አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በጉዳፍ ፀጋይ ላይ የተጣለው ይህ እገዳ ከሰኔ ወር ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ዓመት መስከረም ማብቂያ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
#gudaftsegay #athletics #wada #aiu #running #sportsnews #ethiopianathletics #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa
Source: GetuTemesgen








No comments yet.