የኢትዮጵያ ምስጋና ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የ3 ሳምንታት ታላቅ የምስጋና እና የጸሎት መርሃ-ግብር አዘጋጀች!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja I የኢትዮጵያ ምስጋና ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ከተማ ለቡ አካባቢ ከመንግስት የተሰጣትንና ላለፉት ስምንት ዓመታት በፍርድ ቤት ክርክር ውስጥ የነበረውን 10 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በሕጋዊ መንገድ በይፋ መረከቧን አስታወቀች።

ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚህ አዲስ ይዞታ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ 78ዐኛውን፣ በአዲስ አበባ ደግሞ 7ኛውን አዲስ አጥቢያ በይፋ እንደምትጀምር በዛሬዉ እለት በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ምስጋና ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት መጋቢ ዶ/ር ጌታሁን ነሲቡ በለቡ አጥቢያ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፤ አዲሱ ይዞታ (ለቡ 01 ሆፕ ዩኒቨርሲቲ አጠገብ) በ2010 ዓ.ም ከመንግስት የተሰጠ ቢሆንም፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ባጋጠሙ የተለያዩ ይዞታ ነክ ተግዳሮቶችና ክርክሮች ምክንያት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን ገልፀዉ በአሁኑ ወቅት ግን ተቋሙ ሁሉንም ፈተናዎች በሕጋዊ መንገድ በማለፍ መሬቱን በይፋ ለመረከብ መቻሉን አስታውቀዋል።

በይፋ በተረከቡት አዲሱ ስፍራ ላይ በቀጣይ ታላላቅ የልማት ዕቅዶች እንደሚከናወኑ የተገለፀ ሲሆን ከታቀዱት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል የዘመናዊ አምልኮ እና የቢሮ ሕንጻ ግንባታ፣ ለስነ-መለኮት ኮሌጅ አገልግሎት የሚውሉ ዘመናዊ የተማሪዎችና የአገልጋዮች ማደሪያ ክፍሎች (Dormitories) ግንባታ፣ እና ከአካባቢው ወንዝ ተያያዥነት ያለው የ10 ሺህ ካሬ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የአረንጓዴ ስፍራ ጥበቃ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህን ታላላቅ የልማትና የህንጻ ግንባታ ዕቅዶች ከመጀመሯ በፊት፣ ባለፉት 8 ዓመታት የነበሩትን ፈታኝ የፍርድ ቤት ጉዞዎች በድል እንድትወጣ የረዳትን አምላክ ማመስገን ቀዳሚ ተግባሯ መሆኑን ገልጻ የሦስት ሳምንት ተከታታይ መርሃ-ግብር ማዉጣቷን አስታዉቃለች።

የፊታችን እሁድ ሰኔ 07 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያሉ የቤተ እምነቱ አጥቢያዎች በሙሉ በጋራ በመሆን ሙሉ ቀን የሚቆይ ታላቅ ታሪካዊ የጸሎት እና የአምልኮ ፕሮግራም ያካሂዳሉ።

እሁድ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ የቤተ እምነት መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ልዩ የምስጋና ፕሮግራም ይደረጋል።

ከእሁድ ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በየሳምንቱ እሁድ ከሰዓት በኋላ በዚህ በአዲሱ 7ኛ ለቡ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ የአምልኮ አገልግሎት በይፋ እንደሚቀጥል ታውቋል።

የኢትዮጵያ ምስጋና ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 45 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በወንጌል አገልግሎት እንዲሁም በልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ በስፋት ስትሳተፍ የቆየች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች ላይ ከ780 በላይ አጥቢያዎች እንዳሏት ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል።

ዶ/ር ጌታሁን ነሲቡ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መሳካት አምላካቸውን እያመሰገኑ፣ ክርስቲያኒቱ ጎን ለቆሙ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: