#FastMereja I በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ ‘መጋቢት 2’ በግዛቱ የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን እንዲሆን የቀረበን የውሳኔ ሐሳብ በከፍተኛ ድምጽ አፀደቀ።
ይህ ‘ኤችአር 441’ የተሰኘው የውሳኔ ሐሳብ የፀደቀው ባለፈው ሳምንት በግዛቲቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው።
በአሜሪካ የግዛቶች ምክር ቤት አሠራር መሠረት፣ ይህ ውሳኔ በግዛቲቱ የሕግ መዝገብ ላይ የአድዋ ድል በይፋ ዕውቅና ያገኘበት ታሪካዊ ሰነድ ሆኖ በቋሚነት ይቀመጣል።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ፣ የአውሮፓውያኑ ‘ማርች 2 ቀን 2026’ የ130ኛ ‘የአድዋ ድል ቀን’ ሆኖ በፔንሲልቬኒያ ግዛት ዕውቅና እንዲሰጠው የሚደነግግ ነው።
ውሳኔው በሪፐብሊካን እና በዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች በተሰጠ 195 ከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ እና በ6 ተቃውሞ ብቻ ነው የፀደቀው።
ረቂቁ የቀረበው ከወራት በፊት ቢሆንም የምክር ቤቱን የውስጥ አሠራሮችን አልፎ፣ ውይይቶች ተደርገውበት ከቆየ በኋላ የውሳኔ ድምጽ የተሰጠበት ግን ባለፈው ሳምንት ነው።
”ኤችአር 441” ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡን ለፔንሴልቬኒያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የሰሜን ፊላደልፊያ ሜንገመሪ ካውንቲ፣ የሕዝብ ተወካይ የሆኑት ሴናተር ቤንጃሚን ሳንቼዝ ናቸው።
ቢቢሲ የፀደቀውን የውሳኔ ሐሳብ አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡት ሴናተሩን በኢሜይል ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስኪጠናቀር ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
ሆኖም እርሳቸው ረቂቁን ባቀረቡት ዕለት በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ አድዋ ለአፍሪካ አሜሪካዊያን ያለውን ታላቅ ትርጉም አውስተዋል።
የምክር ቤቱ አባል ሴናተር ቤንጃሚን ሳንቼዝ በዕለቱ በንባብ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር በዘመናዊ የዓለም ታሪክ ውስጥ አድዋ የማይናቅ ቦታ እንዳለው ካወሱ በኋላ “ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ምንሊክ እና ባለቤታቸው ጣይቱ ብጡል በአመራር ሰጪነት አገራቸውን ከቅኝ ገዥ ተቀራማቾች” ማስጣላቸውን አብራርተዋል።
ይህም ለአፍሪካ አሜሪካዊያን፣ በአገረ ግዛቱ ውስጥ ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።
የፔንሲልቬኒያ ግዛት የተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ አውሮፓውያን የአፍሪካ አገራትን ቅኝ ግዛት በያዙበት እና መቼም ነፃ የሚወጡ በማይመስልበት በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን በማስከበር የአደዋ ድልን አድንቋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር በመሆን በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በነበሩ የዓለም ኃያላን ዕውቅና ማግኘቷን ገልጿል።
በመሆኑም የአውሮፓውያኑ መጋቢት 2 በፔንሲልቬኒያ ግዛት “የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን” እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።
“የአድዋ ድል ቀንን በማክበር የአሜሪካን ታሪክንም እናከብራለን” ብሏል።
ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ግንኙነት ላይ የሚሠራው ‘አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ አወድሶታል።
“የፔንሲልቬኒያ ምክር ቤት በውሳኔው ከአድዋ የተቀሰመው ትምህርት ዛሬም ድረስ ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል። በዓለም ሚሊዮኖችን ለሚያነሳሳ እና ለሚያኮራ ለዚህ ታሪካዊ ቀን ዕውቅና በመስጠቱ እናመሰግናለን” ብሏል።
ኮሚቴው ኤችአር 441 ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡን ለፔንሴልቬኒያ ምክር ቤት ላቀረቡት የሕዝብ ተወካይ ቤንጃሚን ሳንቼዝም ምስጋናውን አቅርቧል።
በኮሎራዶ ግዛት የአውሮራ ከተማ ምክር ቤት እንደራሴ እና የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አምሳሉ ፀጋዬ ኤችአር 441′ የተባለው ውሳኔ በምክር ቤቱ ባሉ ሁለቱም ፓርቲዎች [ ዲሞክራት እና ሪፐብሊካን] በከፍተኛ ድምጽ የጸደቀ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ውሳኔው የአውሮፓውያኑ መጋቢት 2 የኢትዮጵያ አርበኞች በ1896 በአድዋ ተራሮች የጣሊያንን ዘመናዊ ጦር ድል ያደረጉበትን ዕለት ለማስታወስ የተላለፈ መሆኑንም አክለዋል።
13 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ፔንሲልቬኒያ ግዛት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያን ፊላዴልፊያን ጨምሮ በሌሎች የግዛቲቱ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ።
“የኢትዮጵያ ታሪክ በኢትዮጵያውያን ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም” ያሉት አቶ አምሳሉ፣ “ያ ታሪክ የአፍሪካውያን እና የጥቁር አሜሪካውያን ታሪክም ጭምር ነው” በማለት፣ የድል ቀኑ በፔንሲልቬኒያ ግዛት እንዲታሰብ መደረጉ ወርቃማ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል።
የአድዋ ድል በተመሳሳይ እርሳቸው በተወከሉበት ኮሎራዶ ግዛት፣ አውሮራ ከተማ ምክር ቤትም ዕውቅና ተሰጥቶት ‘የጥቁሮች ታሪክ ከሚዘከርበት ወር’ ጋር ተጣምሮ የሚከበር በዓል እንደሆነም አስታውሰዋል።
ጉዳዩ ወደ ምክር ቤቱ ከመምጣቱ በፊት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግበት እንደነበር ያወሱት አቶ አምሳሉ “ይህ ታሪካዊ ድል ለኢትዮጵያውያን፣ ለአሜሪካውያን፣ ለጥቁሮች በሙሉ ትልቅ ዕድል ነው” ብለዋል።
በግዛቲቱ ‘መጋቢት 2፣ 2026 ‘ለ130ኛው የዓድዋ በዓል’ መታሰቢያ እንዲሆን ተወሰነ ሲባል ትርጉሙ ምንድነው? ለምንስ ውሳኔው ረዥም ጊዜን ሊወስድ ቻለ በሚል የተጠየቁት አቶ አምሳሉ፣ በምክር ቤት አሠራር የውሳኔ ሐሳቦች (ሪዞሉሽንስ) ብዙ ማለፍ ያለባቸው ሂደት ስላለ ነው ብለዋል።
‘መጋቢት 2’ የአድዋ ቀን መባሉ ደግሞ ለአንድ ጊዜና ለአንድ ዓመት ብቻ ሳይሆን ቋሚና ቀጣይ እንደሆነ አብራርተዋል።
ዕለቱ ለአድዋ ድል መሰየሙ በተግባር ምን ማለት እንደሆነ ተጠይቀው በግዛቲቱ ቀን መቁጠሪያ (ካላንደር) ውስጥ ‘የአድዋ ቀን’ ተብሎ ተካትቶ ታስቦ ይውላል። ይህም ትልቅ ትርጉም ያለው ተዕምርታዊ (ሲምቦሊክ) ነው’ ብለዋል።
ሆኖም ውሳኔው በዚያው ግዛት ተፈፃሚ የሚሆን እንጂ ወደ ፌደራል የሚያመራ እንዳልሆነም አክለዋል።
ይሁንና አድዋ በበርካታ ግዛቶች ዕውቅና እያገኘ ከመጣ፣ ወደፊት ኢትዮ- አሜሪካውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያን እና የተለያዩ አደረጃጀቶች ጉዳዩን በጊዜ ሂደት ወደ ፌደራል ይዘውት እንዲሄዱ አንዳች ዕድል ሊፈጥረ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
አድዋ ኢትዮጵያ በአፄ ምንሊክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ አመራር ሰጪነት የጣሊያን ወራሪዎችን ድል በመምታት ሉዓላዊነቷን አስከብራ የቆየችበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት እና ፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት የሆነ ታሪካዊ ድል ነው።
ከአድዋ ድል በኋላ በርካታ አገራት የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሏቸውን በማጠናከር ለዓመታት በዘለቀ ትግል ነፃነታቸውን መቀዳጀት ችለዋል።
በአፍሪካ ሁለት አገራት ቅኝ አለመገዛታቸውን ታሪክ የሚያስረዳ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ራሷን ያስከበረችው አርበኞቿ ባደረጉ ትግል ነው።
በአድዋ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ሠራዊት አባላት ሲገደሉ ሌሎች ሺህዎች ደግሞ ተማርከዋል። መድፎችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያዎችም መማረካቸውን ታሪክ ያስረዳል።
በተጨማሪም የጣሊያንን ሠራዊት ከመሩት መኮንኖች መካከል ጄነራል አልቤርቶኒ ሲማረክ ዋና አዛዥ ጄነራል ባራቴሪ ሸሽቶ አምልጧል።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ድል የተጎናፀፈችበትን የካቲት 23 ቀንን በየዓመቱ በደማቅ ታሪካዊ ሁነቶች ታከብራለች።
ባለፈው የካቲት ወርም 130ኛው የአድዋ ድል በዓል ተከብሯል። ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው
Source: FastMereja









No comments yet.