#Ethiopia | የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውስጥ ቀዳሚ ባለቤትና አስተዋፅኦ አበርካች መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ የሚያተኩር የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
ይህ የምክክር መድረክ በሀገራዊ ምክክር ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶክተር) የንግዱ ማህበረሰብ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ኢትዮጵያ በርካታ የብዝሀነት ፀጋዎች ያሏት ሀገር ብትሆንም ለረጅም ዓመታት ከግጭት አዙሪት መውጣት አለመቻሏን አስታውሰዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም ኮሚሽኑ ዜጎች ስምምነት ባልደረሱባቸው ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በነፃነት የሚወያዩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል። ተቋሙ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ያላቸው ዜጎች ተሰባስበው ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሄ እንዲያበጁ ለማስቻል የተቋቋመ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ዜጎች በነፃነት የሚመካከሩበትን መድረክ ማመቻቸት፣ የልዩነት መንስኤ የሆኑ አጀንዳዎችን መቅረፅ እና በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን መለየትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም ወገን ያካተተ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አምባዬ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ደረጃ ባሉት መዋቅሮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ገንቢ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በመጥቀስ በቀጣይ በሚካሄደው ዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የህዝቡን ተሳትፎ በማገዝ የባለቤትነት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም ይህንን ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዓይናለም አባይነህ (ዶክተር) በበኩላቸው በሀገሪቱ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የጀመረው ይህ ጥረት ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹና ሳቢ የንግድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ የግሉን ዘርፍ በመወከል ለሂደቱ ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግና የምክክር መድረኮቹ ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲቀየሩ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ፕሬዝዳንቷ አረጋግጠዋል።
#የኢትዮጵያሀገራዊምክክርኮሚሽን #የግሉዘርፍ #ሀገራዊሰላም #ኢኮኖሚ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.