4-1 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ።
#Ethiopia | በስዊዘርላንድ እና በቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና መካከል ትናንት ምሽት የተደረገው ጨዋታ በእግር ኳሱ ዓለም ከፍተኛ ትኩረት እና ትልቅ መነጋገርያ ሆኖ ያመሸ ታሪካዊ ፍልሚያ ነበር።
ጨዋታው በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኛቸው በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የተጫወቱበት ስታዲየም እና የነበረው ድባብ ጭምር ልዩ ትውስታ ጥሎ አልፏል።
በአሜሪካ የሚገኘው እና ይህ ታሪካዊ ጨዋታ የተስተናገደበት ስታዲየም መርሴዲስ ቤንዝ ስታዲየም ነው።
ይህ ስታዲየም በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ልዩ ስሟ አትላንታ በምትባለው ከተማ ውስጥ ይገኛል።
ስታዲየሙ የተገነባው እጅግ ከፍተኛ በሆነ ወጪ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ዋጋው 1.6 ቢሊዮን ዶላር (ወደ 1.600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) ደርሷል። ይህ በዓለም ላይ ካሉ ውድ እና ዘመናዊ ስታዲየሞች አንዱ ያደርገዋል።
በስታዲየሙ ውስጥ እና በዙሪያው እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ከ 2,000 በላይ የደህንነት ሴኪውሪቲ ካሜራዎች ተገጥመውለታል። እነዚህ ካሜራዎች የፊት መለየት ቴክኖሎጂ ያላቸውና የሰዎችን ደህንነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጠብቁ ናቸው ።
ስታዲየሙ እንደ ጨዋታው ዓይነት የመያዝ አቅሙን ማሳደግ የሚችል ሲሆን ለእግር ኳስ ጨዋታዎች በተለመደው ሁኔታ 71,000 ተመልካቾችን ይይዛል። ሆኖም ለትላልቅ ክስተቶች እንደ ዓለም ዋንጫ የመቀመጫ ክፍሎችን በማስፋት እስከ 75,000 ተመልካቾች ማስተናገድ ይችላል።
የስዊዘርላንድ እና የቦስኒያ ጨዋታ በሜዳ ላይ በነበረው ብርቱ ፉክክር በስታዲየሙ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች የፈጠሩት ጩኸት እና ድጋፍ ጨዋታውን ልክ እንደ “የግላዲያተሮች ፍልሚያ” አስመስሎት ነበር።
በዚህ ዘመናዊ ስታዲዮም የስዊዘርላንድ እና የቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና ጨዋታን ለመታደም ከ72,000+ የሚሆን እጅግ ከፍተኛ ህዝብ በስታዲየሙ ተገኝቷል።
ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ትኬቱ Sold Out በመሆኑ ተሽጦ አልቆ የበር ።
ወዳጆቼ ስለስቴዲዮሙ ይህንን ያህል ከነገርኳችሁ ወደ ትናንቱ ምሽት ጨዋታ ልመልሳችሁ ።
ይህ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ የታክቲክ እና የፅናት ፍልሚያ ተብሎ ነው የተሰየመው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኘታቸው ለጨዋታው ልዩ ጉጉት ፈጥሮ ነበር ።
በተለይ በቦስኒያ በኩል ቡድኑ በዓለም ዋንጫ መድረክ አዲስ ታሪክ ለመስራት የነበረው ተነሳሽነት እና የስዊዘርላንድ ልምድ ያለው ስብስብ መጋጠማቸው ጨዋታውን ማራኪ አድርጎታል።
በስዊዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያሉ በርካታ ተጫዋቾች ለምሳሌ እንደ ጃካ እና ሻኪሪ ያሉ የባልካን አካባቢ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የስደተኞች ትውልድ በመሆናቸው ጨዋታው ከስፖርታዊ ገፅታው ባለፈ ጥልቅ ስሜት እና ማህበራዊ ትስስር የነበረው በመሆኑ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል።
ስዊዘርላንድ በጨዋታው ላይ የበላይነቱን እንድትይዝ እና 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት እንድታሸንፍ ያደረገው ትልቁ ምስጢር የቴክኒክ ክፍሉ ያደረገው የተጫዋቾች ቅያሬ ነው።
ከመጠባበቂያ ወንበር የተነሱት የስዊዘርላንድ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ እንደገቡ ያሳዩት ፍጥነት ጉልበት እና ለማመን የሚያስቸግር የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ወደ እነሱ እንዲያደላ አድርጎታል።
የቦስኒያን የመከላከል መስመር በመበጣጠስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግቦችን ማከታተል የቻሉበት መንገድ የስዊዘርላንድን የተጫዋቾች ስብስብ ጥራት በግልፅ ያሳየ ነበር።
በአንጻሩ ለቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና ጨዋታው መጥፎ መልክ መያዝ የጀመረው ተጫዋቻቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበት ቅጽበት ጀምሮ ነው።
በአለም ዋንጫ መድረክ ላይ ያውም እንደ ስዊዘርላንድ ካለ ልምድ ያለው እና በታክቲክ ከበሰለ ቡድን ጋር በጎደሎ በ10 ተጫዋች መጫወት እጅግ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ነበር።
ቀይ ካርዱ በፈጠረው ክፍተት ምክንያት የቦስኒያ ተጫዋቾች ሜዳውን ሙሉ በሙሉ መሸፈን አቅቷቸው ለከፍተኛ ድካም ተጋልጠዋል። ስዊዘርላንዶችም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው በ20 ደቂቃ ውስጥ ግቦቹን ማዝነብ ችለዋል።
ባጠቃላይ ጨዋታው የስዊዘርላንድን ታክቲካዊ የበላይነት እና የተጫዋቾች ቅያሬ ስኬታማነት ያሳየ ሲሆን ለቦስኒያ ደግሞ ቀይ ካርድ በአንድ ትልቅ ጨዋታ ላይ ምን ያህል ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል ያስመሰከረ የቁጭት ምሽት ሆኖባቸዋል።
ታዋቂ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ኮሜንታተሮች እንደ Peter Drury እና Martin Tyler ያሉ የጨዋታውን ድባብ በደመቀ ቃላት አጋነውታል።
”ይህ ጨዋታ የእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን የታሪክ የፅናት እና የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ነው!” በማለት ኮሜንታተሮች የቦስኒያን ስብስብ “የማይበገሩ እና ለሀገራቸው ክብር የሚጫወቱ አናብስት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። በዓለም ዋንጫው መድረክ አዲስ ቢሆኑም ያሳዩት ድፍረት እና በኤዲን ጄኮኍ የሚመራው ማጥቃት የሚደነቅ ነበር።
ስዊዘርላንዶች ጨዋታውን በተረጋጋ ሁኔታ መቆጣጠራቸውንና እንደ ሰዓት ትክክለኛ በሆነው የታክቲክ ስነ-ስርዓታቸው ጨዋታውን መምራታቸውን አድንቀዋል።
አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
Source: GetuTemesgen









No comments yet.