አዲሱ ”ኢት AAA 0000” ታርጋ በቴስላ ተያዘ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | አዲሱን 0000 የታርጋ ቁጥር የወሰደችው የቴስላ ሞዴል ዋይ መኪና ባለቤት ሰሌዳዋን በኬክ ቆርሳ ስነ-ስርዓት ተረክባለች፡፡ ለዓመታት በቶዮታ ራቭ-ፎር ተሸከርካሪ ተይዞ የቆየው ክብረ-ወሰንም ተሰብሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲሱ የተሸከርካሪ ሰሌዳ የመጀመሪያ ተጠቃሚ ለመሆን የበቃችው የቴስላ ሞዴል ዋይ መኪና ባለቤት ሌሎች ወጪችን ሳይጨምር መነሻ ዋጋ 44,500 ብር በመክፈል ታርጋዋን የተረከበች ሲሆን፣ በዕለቱም ከእርሷ ጋር አብረው ሌሎች በቅደም ተከተላቸው ታርጋ የወሰዱ አሽከርካሪዎች በአዲስአበባ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኬክ የመቁረስ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል፡፡

አዲሱ ታርጋ ሲወጣ መነሻ ቁጥሩ 0001 ይጀምራል ተብሎ ቢገመትም፣ የመጀመሪያዋ ቴስላ ሞዴል ዋይ ተሽከርካሪ የወሰደችው ቁጥር ግን አራት ዜሮ ወይም 0000 ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህ አዲስ ታርጋ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 800 ሺህ ገደማ የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ የሚነገር ሲሆን ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ የኮድ 2 ወይም የቤት መኪናዎች ናቸው።

በእነዚህ የቤት መኪናዎች ታሪክ ውስጥ አንደኛ ቁጥርን በመያዝ ኮድ 2 – 00001 በመሆን ለረጅም ዘመናት ስትታወቅ የኖረችው ቶዮታ ራቭ-ፎር Toyota RAV4 ተሽከርካሪ ታሪካዊ የአንደኝነት ስፍራዋን ለቴስላዋ ተሸከርካሪ ማስረከቧ እርግጥ ሆኗል።

በጉዳዩ ዙሪያ በአርትስ ቴሌቪዥን የካሪቡ አውቶሞቲቭ ፕሮግራም ላይ የዘርፉ ባለሞያዎች በሰጡት አስተያየት ይህ የአንደኝነት ደረጃ መኪናው ሀገር ውስጥ የገባበትን ቅደም-ተከተል ሳይሆን አዲሱ የታርጋ ለውጥ በተደረገበት ወቅት ሰሌዳውን ቀድሞ የመውሰድ አጋጣሚን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ማንኛውም ባለሃብት ወይም የተሽከርካሪ ባለቤት የፈለገውን ልዩ ቁጥር፣ ስሙን ወይም የተለየ ምልክት በሰሌዳው ላይ እንዲካተትለት ከፈለገ፣ ከተቀመጠው መደበኛ ተመን በተጨማሪ የተለየ ክፍያ በመክፈል የራሱን ልዩ ታርጋ መውሰድ የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል ተብሏል።

የተሽከርካሪ ባለቤቶች አዲሱን ታርጋ በየተራቸው እንዲቀይሩ ጥሪ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ አሰራሩ ከተለመደው ኮድ 1፣ ኮድ 2 እና ኮድ 3 አከፋፈል ወጥቶ ሁሉንም በአንድ የቁጥር መለያ ስር የሚያጠቃልል መሆኑ ታውቋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2