♦️
♦️የጀርመንና የኮትዲቯር የዛሬ ጨዋታ ትኬት ጥብስ ሆኗል
♦️ከ5ሺ በላይ የጀርመን ደጋፊዎች የቶሮንቶን ጎዳና አጣበዋል
#Ethiopia | አቤት ጊዜው እንዴት ይሮጣል?ዕድሜም ሳይታወቀን ላፍ ይላል፤ ልክ በዛሬው ቀን June 20/2010 በፊፋ የምስረታ ታሪክ ከ102 ዓመታት ጥበቃና ትዕግስት በኋላ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በ2010ሩ የዓለም ዋንጫ የዲዲዬ ድሮግባዋን ኮትዲቯርን በደቡብ አፍሪካው ግዙፍ ስታዲየም ሶከር ሲቲ ስታዲየም ከብራዚል ጋር ያደረጉትን ጨዋታ በአካል ተገኝቼ ከተመለከትኩ ድፍን 16 ዓመት ሞላው።
ዛሬ ደግሞ ኮትዲቯር በብራዚል 3ለ1 የተሸነፈችበትን፣ዲዲዬ ድሮግባ ከሽንፈት ያላዳነች ግብ ያስቆጠረበት፣በዕምነቱ ጠንካራ የሆነው የመሀል ሜዳው ሞተር ብራዚሊያዊው ካካ ድንቅ ጨዋታውን ብቻ ሳይሆን አመለ ቢስ ሆኖ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደበት፣ሉዊስ ፋቢያኖ ሁለት ጎል ሲያስቆጥር በሶከር ሲቲ ስታዲየም ተገኝቼ የታደምኩበት ጨዋታ በታሪክ ግጥጥሞሽ ከ16 ዓመታት በኋላ ኮትዲቯር ከ ጀርመን የምታደርገውን ጨዋታ ለመመልከት ለሚዲያ በተዘጋጀው አውቶብስ(Shuttle Bas)በBMO Field ቶሮንቶ ስታዲየም ድንገት የተከሠተ ኢትዮጵያዊ ሆኛለሁ።
ምን ውጤት ይመዘገባል? የሚለውን ለጊዜው ላቆየውና ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ኮትዲሻርን ያየሁበት June 20/2010 ዛሬ መልኩን፣ ሀገሩን፣ስታዲየሙንና ተጋጣሚውን ቀይሮ ኮትዲቯር በአዲሱ ትውልድ የምታደርገውን ፍልሚያ ከ16 ዓመታት በኃላ ሊያሳየኝ የሠዓታት ቀጠሮ ይዞልኛል፤አይ የቀን መገጣጠም ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
♦️ስለ ጀርመንና ኮትዲቯር ጨዋታ 10 ነጥቦች በእግረ መንገድ
👉ተጠባቂውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ የፓራጓይ ዜግነት ያላቸው የ43 ዓመቱ ጆዋን ጋብርኤል ቤኒቴዝ በመሃል ዳኝነት ይመሩታል፤እኚህ የአለም ዋንጫን ሲመሩ የመጀመሪያቸው ነው
👉ከ5,000 በላይ የጀርመን ደጋፊዎች ቶሮንቶ መግባታቸውን ተከትሎ የስታዲየሙ ድባብ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ ያለው ድባብም ተቀይሯል፤ሌክ ሾርና ባትረስ ስትሪቶች ላይም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና የመንገዶች መዘጋጋት ተፈጥሯል፤ነውጠኞቹ የጀርመን ደጋፊዎች ቶሮንቶ ስታዲየምን በድጋፍ ይንጡታል።ከጨዋታው በፊትም የጀርመን ብ/ቡድን ያረፈበትን ሆቴልም ከበው ሲያጨናንቁ፣የተያዩ ጎዳናዎችንም ሲያጣብቡ ተስተውሏል፤
👉የዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የትኬት ዋጋ የሚቀመስ አልሆነም፤ትኬቶች ሙሉ በሙሉ ተሸጠው ማለቃቸው እየተነገረ ሲሆን የትኬቶች ዋጋ ከ1043 እስከ 6,732 የካናዳ ዶላር(ከ166ሺ -1ሚሊዮን 77ሺ እንዲሁም በሌላ አማራጭ ከ227ሺ እስከ 1ሚሊዮን 104ሺ የኢትዮጵያ ብር)ድረስ ዋጋ የሚያወጡ መሆናቸው ብዙዎችን አነጋግሯል
👉በ2009 በዋናው ብ/ቡድን ተገናኝተው 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ከተለያዩ በኋላ ዛሬ በአለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ቶሮንቶ ላይ ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
👉በወዳጅነት ጨዋታ 2ለ2 ሲለያዩ ከአራቱ ጎሎች ሶስቱን ለየሀገራቸው ያስቆጠሩት የአርሰናልን ማልያ ለብሠው የተጫወቱት ሉካስ ፖዶሎስኪ(2)፣ኢማኑኤል ኤቡዬ(1) ናቸው
👉ሁለቱም ቡድኖች የምድባቸውን ሁለተኛ ጨዋታ የሚያደርጉት በአሸናፊነት የድል ስሜት ውስጥ ሆነው ነው ጀርመን ኩራካኦን 7ለ1 ኮትዲቯር ኢኳዶርን በአስገራሚ የመጨረሻ ሠዓት ድል 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋየውን አስፍተው ነው የሚገናኙት
👉የማሸነፍ ግምቱን ለአራት ጊዜ የአለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን ቢሠጥም ኮትዲቯር ቀላል ተፎካካሪ እንደማትሆን እየተነገረ ነው፤እንደ Opta የጨዋታ ግምት ከሆነ የአሸናፊነቱን ቅድሚያ 44.2% በመስጠት ቀዳሚ አድርጓቷል
👉የጀርመን ተጫዋቾች ዛሬ ከአይቮሪኮስት ጋር ከሚያደርጉትን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ቀደም ብሎ ቶሮንቶ ሲደርሱ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ተደርጎባቸዋል፤ተጫዋቾቹ ከጀርባም ከፊትም ጥብቅ በሆነ የደህንነት ፍተሻ ሲደረግባቸው መታየቱ ከጨዋታው በፊት የብዙዎች የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርጎአቸዋል
👉ወደ ካናዳ ይገባል አይገባም በሚል ሲያከራክር የቆየው የኮትዲቯሩአጥቂ ኤልዬ ዋሂ ካናዳ የመግባት ፍቃድ በማግኘቱ በኋላ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል፤ፈረንሳይ የተወለደው የ23 ዓመቱ ኤልዬ ዋሂ ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ መመለሱ ለአጥቂው ክፍል ጥንካሬ ወሳኝነት ስላለው የካናዳን መሬት እንዲረግጥ ፍቃድ ማግኘቱና ቡድኑን መቀላቀሉ ብዙዎችን አስደስቷል፤የቀድሞ የኢንትራክት ፍራንክፈርት ኤልዬ ዋሂ ወደ ፈረንሳዩ ኒስ በትውስት ተሠጥቶ በሊግ 1 በመጫወት ላይ ይገኛል
👉ሁለቱ ቡድኖች በፊፋ የወሩ ደረጃ(Ranking)ጀርመን 9ኛ፣ኮትዲቯር 30ኛ ደረጃን ይዘው የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ነው
✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከከናዳ ቶሮንቶ ስታዲየም

Source: GetuTemesgen








No comments yet.