ወደ ሞንትርያል የሚያሻግረው ትልቁ የብስክሌት ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከጆርካ ኤቨንት ጋር በመተባበር ከሰኔ 17 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ደማቅ አገራዊ የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድርን ሊያካሂድ ነው። ይህ ስፖርታዊ ክስተት በካናዳ ሞንትርያል ለሚካሄደው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ምርጥ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ወሳኝ የማጣሪያ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።

​ከመላው ሀገሪቱ እንዲሁም ከተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች የተውጣጡ ከ200 በላይ ብስክሌተኞች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ውድድር፣ ስፖርተኞቹ በታይም ትራያል (Time Trial) እና በሮድ ሬስ (Road Race) ዘርፎች ይፋለማሉ። በአዲስ አበባ የውድድር መስመሮች ላይ በሚደረገው በዚህ ፉክክር፣ ወጣቶችና አዋቂዎች በሁለቱም ፆታዎች ብቃታቸውን የሚያሳዩ ሲሆን የሀገሪቱን ምርጥ ተወዳዳሪዎች በአንድ የሚያሰባስብ ትልቅ መድረክ ነው።

​ይህ የብሔራዊ ሻምፒዮና ውድድር ለኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት እድገት የጎላ ፋይዳ ያለው ከመሆኑም ባሻገር፣ አትሌቶቹ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሸጋገሩና ፕሮፌሽናል ክለቦችን በመቀላቀል ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች ናቸው፤ በተለይም የ2017 ዓ.ም የወንዶች ዘርፍ ሻምፒዮን የሆነው ተክለ ፀጋይ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረኮች ባሳየው አስደናቂ ብቃት የቻይና ፕሮፌሽናል ክለብን መቀላቀል መቻሉ፣ እንዲሁም በሴቶች ዘርፍ ታዳጊዎች የጀርመን ፕሮፌሽናል ክለብን እንዲቀላቀሉ በር መከፈቱ የውድድሩን ትልቅነት ያሳያል።

​በዓለም አቀፉ የብስክሌት ፌዴሬሽን (UCI) አዘጋጅነት ከ201 ሀገራት የተውጣጡ ምርጥ አትሌቶች በሚሳተፉበት የዓለም ሻምፒዮና ላይ መገኘት ለሙያ ዕድገት፣ ለዓለም አቀፍ ዕውቅና እና ታላላቅ ክለቦችን ለመቀላቀል ወሳኝ እርምጃ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን መላው የስፖርት አፍቃሪዎች፣ አጋር ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በዚህ አገራዊ ኹነት ላይ በመታደም ተወዳዳሪዎቻችንን እንዲያበረታቱ ጥሪውን አስተላልፏል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1