በቅሚያ ወንጀል ተከሶ የ3 ዓመት ፍርድ ውሳኔውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት በወጣ በ3ኛው ቀን የስርቆት ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በፅ

- Advertisement -
Sidebar AD

በቅሚያ ወንጀል ተከሶ የ3 ዓመት ፍርድ ውሳኔውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት በወጣ በ3ኛው ቀን የስርቆት ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ።

ዳዊት በላቸው የተባለው ተከሳሽ ከዚህ ቀደም የቅሚያ ወንጀሉን የፈፀመው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው አረንጓዴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ/ም ነበር።

ግለሰቡ የዋጋ ግምቱ 25 ሺህ ብር የሚያወጣ ሳምሰንግ M 32 ሞባይል ከግል ተበዳይ ላይ ቀምቶ ለማምለጥ ሲሞክር በፖሊስ አባላትና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፈንጅ ተይዞ አስፈላጊውን ምርመራ ከተጣራበት በኋላ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበት ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ወንጀል ችሎት በ3 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበት በማረሚያ ቤት መቆየቱን በክፍለ ከተማው ፖሊስ ዋና መምሪያ የቤተል አካባቢ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የ3 አመት የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት የወጣውና ያልታረመው ይህ ግለሰብ በወጣ በ3ኛው ቀን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቤተል አካባቢ ከሚገኝ አንድ አፖርታማ ገብቶ 19 ሺህ ብር የሚገመቱ የተለያዩ ጫማዎችን ሰርቆ ለማምለጥ ሲሞክር ስራ ላይ በነበሩ የወንጀል መከላከል የፖሊስ አባላትና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፈንጅ መያዙን የቤተል አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

የተሰረቁት ንብረቶች በኤግዚቢት ተይዘው በግለሰቡ ላይ አስፈላጊው ምርመራ ከተጣራበት በኋላ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፤ ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ፈጣን ወንጀል ችሎት ተከሳሹን ያስተምራል ሌሎች ወንጀል ፈፃሚዎችን ያስጠነቅቃል በማለት ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ/ም በዋለው ችሎት በፈፀመው ደጋጋሚ የወንጀል ድርጊት በ4 አመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ እንዳስተላለፈበት ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

አብዛኛው ወንጀል ፈፃሚ በማረሚያ ቤት የእስር ቆይታው በጥሩ ስነ ምግባር ታርሞና ታንፆ ወደ ማህበረሰቡ ቢቀላቀልም አንዳንድ የእጅ አመል ያለባቸው ግለሰቦች ደግሞ ከማረሚያ ቤት ወጥተው ወንጀል ቢፈጽሙም ከህግ እንደማያመልጡ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ህብረተሰቡ ወንጀል እንዳይፈፀምበት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: