ሴኔጋል በድጋሚ ተሸነፈች
#Ethiopia | በ23ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ዘጠኝ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ፈረንሳይና ኖርዌይ ወደ ጥሎ ማለፍ መሸጋገራቸውን ሲያረጋግጡ፣ ሴኔጋል ደግሞ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈቷን ተከናንባለች።
ኖርዌይ ከሴኔጋል ጋር ባደረገችው ጨዋታ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ድል ቀንታለች። ለኖርዌይ ማርከስ ፔደርሰን አንድ ግብ ሲያስቆጥር፣ ኧርሊንግ ሀላንድ ደግሞ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑን ድል አረጋግጧል። ለሴኔጋል ኢስማኤሊያ ሳር ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ቢኖሩም ቡድኑን ከሽንፈት ማዳን አልቻሉም።
በሌላኛው የምድቡ ጨዋታ ፈረንሳይ ኢራቅን 3 ለ 0 በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝታለች። ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፣ የባሎንዶር አሸናፊው ኡስማን ዴምቤሌ ደግሞ ሦስተኛዋን ግብ አክሏል።
በእነዚህ ውጤቶች ኖርዌይና ፈረንሳይ ከምድብ ዘጠኝ ወደ ጥሎ ማለፍ መሸጋገራቸውን በይፋ አረጋግጠዋል። ሴኔጋል ግን በመጨረሻው የምድብ ጨዋታዋ ከኢራቅ ጋር በምታደርገው ፍልሚያ በምርጥ ሦስተኛነት ለማለፍ ያላትን ጠባብ ዕድል ለመጠቀም ትሞክራለች።
በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ደግሞ ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሀላንድ እያንዳንዳቸው አራት ግቦችን በማስቆጠር ውድድሩን እየመሩ ሲሆን፣ ቀጣዮቹ ጨዋታዎች የወርቃማ ጫማ ፉክክሩን የበለጠ አስደሳች ያደርጉታል።

Source: GetuTemesgen









No comments yet.