እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከ2,800 በላይ ተማሪዎችን ነገ ያስመርቃል

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | እንጅባራ – እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ (አረንጓዴው ግቢ) ለ7ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 2,812 ተማሪዎች ነገ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንደሚያስመርቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በ52 የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የሚያስመርቅ ሲሆን፣ ከተመራቂዎቹ ውስጥ 40 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

የዘንድሮውን የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ለየት ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ዩኒቨርሲቲው በአንስቴዢያ፣ በሶፍትዌር ምህንድስና፣ በአገወኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም በመምህራን ትምህርትና ካሪኩለም ዘርፎች በአዳዲስ ፕሮግራሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ተመራቂዎችን ማፍራቱ ይገኝበታል።

ፕሬዝዳንቱ እንዳስረዱት፣ የአገወኛ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ጥናትና ልማት የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ የትኩረት መስኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገወኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራሞች የሰለጠኑ 150 ተማሪዎችን ያስመርቃል።

የምረቃ ፕሮግራሙ በአሚኮ የቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ሲሆን፣ በመርሃ ግብሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና አርቲስቶች እንደሚገኙም ተገልጿል።

በመጨረሻም ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ ለተማሪዎቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጉ መምህራን፣ ሠራተኞች እና የአካባቢው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1