የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ላይ ጠንካራ የተቃውሞ መግለጫ አወጣ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ዋና የስራ አስኪያጅ፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሰራተኞች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጋራ በመሆን በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ላይ ያነጣጠረ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። ሀገረ ስብከቱ ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ባሰራጨው በዚህ መግለጫ፣ የአሁኑ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ዘካርያስ በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት መዋቅርና አስተዳደር ላይ ጣልቃ እየገቡ ነው ሲል በፅኑ ኮንኗል።

የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ባወጣው ዝርዝር መግለጫ እንዳመለከተው፣ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ በህገ ቤተ ክርስቲያን ከተሰጣቸው የስልጣን ክልል ውጪ በመውጣት በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ በተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት እየፈጸሙ ይገኛሉ። ሊቀ ጳጳሱ በደብዳቤና በነጻ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች (ፌስቡክን ጨምሮ) የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚንዱ፣ የግል ጥቅምና ጥላቻን ያዘሉ ናቸው ሲል መግለጫው ወቅሷል።

በተጨማሪም አቡነ ዘካርያስ ቀደም ሲል በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በነበራቸው የስራ ቆይታ ወቅት የገንዘብ ብክነትና የስራ አመራር ጉድለት ፈጽመዋል ተብሏል። በዚሁ መነሻነት በቅዱስ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ኦዲት ተደርጎ በተረጋገጠው መሰረት፣ ከተጠየቁት 3 ሚሊዮን ብር ውስጥ 1.6 ሚሊዮን ብር የከፈሉ ቢሆንም ቀሪውን 1.4 ሚሊዮን ብር ከነወለዱ ለሀገረ ስብከቱ ገቢ እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ግፊት እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

መግለጫው አክሎም፣ ሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላኩ ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት የቀደሱትን የደብረ ኢየሱስ ገዳም ታሪካዊ ካቴድራል “አይቆጠርም፣ እንደገና ይባረካል” በማለት የጻፉት ደብዳቤና ጥምቀትን በተመለከተ የሰጡት አቋም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና መመሪያ የጣሰ ነው ብሏል። በዚህም ምክንያት የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት መዋቅር፣ መላው የጎጃም ካህናትና ምዕመናን ከብፁዕ አቡነ ቶማስ ጎን በመቆም የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአቡነ ዘካርያስ ህገ-ወጥ በተባሉ ድርጊቶች ላይ ተገቢውን የህግና የስርዓት እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄውን አቅርቧል።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1