ዶክተር መቅደስ ዳባ
#Ethiopia | የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው ዓመት ከሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ደግሞ አራተኛ ደረጃን በመያዝ የልህቀት ጉዞውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ።
በዛሬው እለት የጎንደር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች የምረቃ በዓል መርሐግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከቅድመ አንደኛ እስከ ከፍተኛ የዶክተራልና ሰብ-ስፔሻሊቲ ደረጃ ድረስ የትምህርት አድማሱን ያሰፋ ግዙፍ ማዕከል ለመሆን በቅቷል።
በአሁኑ ወቅት ሰፊ ተቋማዊ ሪፎርም እያካሄደ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፈር ቀዳጅነት የተጀመረውና ተቋሙን ሁለንተናዊ ራስን የመቻል አቅም የሚያጎናጽፈው ወደ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት የመሸጋገር ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አብስረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው ዓመት ከሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ደግሞ አራተኛ ደረጃን በመያዝ የልህቀት ጉዞውን አጠናክሮ መቀጠሉን በትምህርት ጥራትና በሁሉም ተደራሽ በሆነ አካታች ስራ የተመዘገበ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ የጎንደር ህዝብ እንግዶችን አቅፎና መርቆ የመሸኘት ታላቅ ባህል ያለውን እሴት በማንሳት ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ተቋም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዘመናዊ የጤና ትምህርትና የባለሙያ ልማት መፍለቂያ፣ እንዲሁም በሪፈራል ሆስፒታሉ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በተለያዩ ልዩ የህክምና ዘርፎች የሚታደግ የሰብአዊነትና የበጎ አገልግሎት ተምሳሌት መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
አዲስ ተመራቂዎችም በትምህርት ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀት ብቻ ሳይሆን የተቋሙን መለያ የሆነውን ሰብአዊነት፣ ታማኝነትና ደግነት በተግባር በማሳየት ማህበረሰባቸውንና ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም፣ ዘመኑ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በቴክኖሎጂ ፍጥነት እየተቀየረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ ተመራቂዎች የዓለምን የእድገት ደረጃ በመከተል ራሳቸውን ዘወትር በዕውቀት እንዲያጎለብቱና የጣለባቸውን ተስፋ በተግባር እንዲያለመልሙ መልዕክት ተላልፏል።
ጌትነት ተመስገን
ከጎንደር
#getutemesgen #getu #ጌጡ
#UoGGraduation #UniversityOfGondar #EthiopianEducation #Autonomy #Graduation2018




Source: GetuTemesgen









No comments yet.