ሰኔ 18 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት በደረሰኝ በመግዛትና በመሸጥ፣ በግብር አከፋፈል፣ በህግ ተገዢነት ደረጃ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ 3 ታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሽልማት ሰጠ
በዛሬው ዕለት በከተማችን ትልቁ የገበያ ስፍራ በሆነው በመርካቶ በተዘጋጀ የእውቅና መርሀ ግብር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቡድልቃድር ሬድዋን ቢሮው የታክስ ህግን አክብረው የሚሰሩ ግብር ከፋዮች ለሌሎች አርአያነት ባለው መልኩ እውቅና መስጠቱ የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ሁሉም ግብር ከፋይ ጤነኛ የደረሰኝ አጠቃቀም ባህል በማዳበር የህግ ተገዢነት ደረጃውን ለማላቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ይበልጥ መደገፍ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁነ ወቅት በከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት የግብር ከፋዮች ሚና የላቀ መሆኑን በመግለፅ ይህ እንዲጠናከር ህገወጦች ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ከመቅጣት ባሻገር በህጋዊ መንገድ የሚሰሩትን ደግሞ ማበረታታት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በበኩላቸው ቢሮው በከተማዋ ክብርት ከንቲባ በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ከግብር ከፋዮች ጋር ተቀራርቦና ተጋግዞ ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የዕለቱ በደረሰኝ ግብይት የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ፕሮግራምም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሀላፊው አክለውም የእውቅና ፕሮግራሙ የግብር ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ለሚገኙ፣ በግዢና በሽያጭ ወቅት ደረሰኝ በአግባቡ ለሚጠቀሙ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታት መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም መሰል የታማኝ ግብር ከፋዮች፣ የሸማቾችና በ7075 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ የሚሰጡ ነዋሪዎች የእውቅና መርሀ ግብሮች ተጠናክሮ የሚቀጥሉ መሆናቸውን በመግለፅ ሸማቹ ማህበረሰብም የከተማዋ ልማት ይበልጥ እንዲጠናከር ግብይቱን በደረሰኝ ብቻ በመፈፀም የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሀመድ በበኩላቸው ቢሮው በአሁኑ ወቅት ከግብር ከፋዮች ጋር ተቀራርቦ በመስራት፣ የግብር ከፋዮችን ችግር በማድመጥ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብም ህጋዊነትን በማጠናከር፣ በደረሰኝ የመገበያየት ባህል በማዳበር በሁሉም አቅጣጫ እየተፋጠነ ባለው ለከተማዋ ልማት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
በተጨማሪም ህገወጦችን ወደ ህጋዊነት ለመመለስ ማስተማር እንዲሁም የህግ ተገዢነት ደረጃቸው የተሻለ የሆነውን ደግሞ የማበረታታትና እውቅና የመስጠት ተግባሩ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በዕለቱ በደረሰኝ ግዢ በመፈፀምና በመሸጥ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ 3 ግብር ከፋዮች የሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ተበርክቷል፡፡



Source: FastMereja








No comments yet.