#Ethiopia | ጄኔቫ፣ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. – ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን በምታካሂደው የድርድር ሂደት አካል የሆነውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ፕሮቶኮል (Bilateral Market Access Protocol) ከኒውዚላንድ ጋር ተፈራርማለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፉ የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት ለመቀላቀል በምታደርገው ጉዞ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል። ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረውን የሁለትዮሽ ድርድር ያጠናቀቀው ይህ ፕሮቶኮል፣ በሸቀጦችና በአገልግሎቶች ዘርፍ ላይ የጋራ የገበያ ተደራሽነት ግዴታዎችንና ጥቅሞችን ያካትታል።
ስምምነቱን በጄኔቫ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው እና በWTO የኒውዚላንድ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ክሌር ኬሊ ፈርመውታል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ሁለቱ አገራት ግልጽነትን፣ በሕግ የሚመራ ሥርዓትን እና ልማትን ማዕከል ያደረገ የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የኒውዚላንድ ተወካይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች አገር መሆኗን በማንሳት፣ የWTO አባል መሆኗ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። በተጨማሪም አገራቸው የኢትዮጵያን የWTO አባልነት ሂደት በመደገፍ ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለች።
አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው በበኩላቸው፣ ኒውዚላንድ በድርድሩ ሂደት ሁሉ ላሳየችው ገንቢ ተሳትፎ እና ቀጣይነት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ከንግድ ግንኙነቱ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ እና ኒውዚላንድ በግብርና፣ በጂኦተርማል ኃይል ልማት እና በቴክኒክ አገልግሎቶች ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እያጠናከሩ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።
Source: GetuTemesgen









No comments yet.