#Ethiopia | የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያስተምራቸው የቆዩ 758 ተማሪዎችን ለ15ኛ ጊዜ አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች፣ በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽን እና በክረምት ፕሮግራሞች ሲያስተምራቸው የቆዩ ተማሪዎችን በተመራቂዎች ቤተሰቦችና በተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሥነ-ስርዓት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን አበጋዝ፣ ተመራቂዎቹ ከብዙ ጥረትና ትጋት በኋላ ለዚህ ደረጃ መብቃታቸውን አድንቀው፣ ምረቃ የሕይወት አዲስ ምዕራፍ እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ተመራቂዎችም በሙያቸው ውጤታማ ለመሆን እና ለአገር ልማት አስተዋፅኦ ለማበርከት በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት አገልግሎት በተጨማሪ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ጉልህ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ የደብረታቦር ከተማ ህዝብ ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በምረቃው ልዩ ትኩረት የሳቡት ከደቡብ ሱዳን በትምህርት ዕድል መጥተው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ የተማሪዎቹ ተወካይ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳገኙ ገልጻለች። በቆይታቸውም የኢትዮጵያን ባህልና እሴቶች ማወቅ እንደቻሉ ጠቅሳ፣ ይህንን ልምድ ወደ አገራቸው ይዘው እንደሚመለሱ ተናግራለች።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ከየኮሌጁና ከየኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፣ ከሴት ተመራቂዎች መካከል የሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ ዲፓርትመንት ተማሪ እየሩስ ተቀባ 3.9 ነጥብ በማስመዝገብ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች።
በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት ባለቤት የሆነው የሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ ተማሪ አሸናፊ ታከለ 3.97 ነጥብ በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስመርቋል።
– ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን



Source: GetuTemesgen









No comments yet.