በጎፋ ዞን የ6 ወር ነፍሰ ጡር ባለቤቱን በግፍ የገደለው ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነበት

- Advertisement -
Sidebar AD

የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት፣ የገዛ ባለቤቱንና የልጆቹን እናት በአሰቃቂ ሁኔታ በጭካኔ በገደለ ተከሳሽ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል። ሟች በወቅቱ የ6 ወር ነፍሰ ጡር እንደነበረች ተገልጿል።

በዞኑ ላሃ ከተማ አስተዳደር ሀብት-ምንጭ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመውን ይህን ድርጊት አስመልክቶ የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሹ አቶ ጀማል ሁሴን ከባለቤቱ ጋር በነበራቸው የፍትሐብሔር ክስ ምክንያት ቂም በመያዝ ጥቃቱን ፈጽሟል።

ተከሳሹ “ለምን በሕግ ከሰስሽኝ” በሚል የበቀል ስሜት ተነሳስቶ ስለታማ ቢላዋ በመጠቀም በሟች ፊት፣ ጭንቅላትና አንገት ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከባድ የቁስል ጉዳት በማድረስና ከጀርባዋ አንገቷን በማረድ ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።

በዚህም መሠረት ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1) (ሀ) ስር በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ከስሶታል።

ክሱን የመረመረው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የወንጀሉን መፈጸም ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ ማስረዳታቸውን በማረጋገጥ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ የሚያስተባብል ምንም ዓይነት የመከላከያ ማስረጃ የለኝም ማለቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በጥፋተኝነት ፈርዶበታል።

በመጨረሻም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ያደመጠው ችሎቱ፣ የወንጀሉን ከባድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 03/2017 መሠረት በእርከን 45 ስር ባለው የዳኝነት ሥልጣን ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣ በዛሬው ዕለት ወስኗል።

Via ጎፋ ዞን ኮሙኒኬሽን



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1