‎” እኛ የዚህች ምድር ጠባቂዎች ነን ! “

- Advertisement -
Sidebar AD


‎ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን

‎#Ethiopia | ​ታዋቂው የቅሪተ አካል ተመራማሪና የ”ሉሲ” (ድንቅነሽ) አግኝ ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን በኢትዮጵያ ውስጥ የሰውን ልጅ አመጣጥ በመመርመር ላበረከቱት የግማሽ ክፍለ ዘመን አስተዋጽኦ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዶክተር ኦፍ ፊሎሶፊ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ተሰጣቸው።

‎ፕሮፌሰሩ ከዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ካሊፎርኒያ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ ይህንን ልዩ የክብር ማዕረግ በትልቅ ትህትና እንደሚቀበሉትና በአካዳሚክ ሕይወታቸው ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ እንደሆነ በመግለጽ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይንና ለፋኩልቲ አባላት ያላቸውን የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

‎​ፕሮፌሰር ጆሃንሰን እ.ኤ.አ በ1970 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ታችኛው የኦሞ ሸለቆ በመምጣት የጀመሩትን የጥናት ጉዞ ያስታወሱ ሲሆን፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የቅሪተ አካል ጥናት መሠረተ ልማትም ሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳልነበረ ገልጸዋል።

‎ዛሬ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ላቦራቶሪዎችን በመገንባቱ በርካታ የውጭ ምሁራንና ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የሀገር ውስጥ ተወላጅ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በዘርፉ በስፋትና በውጤታማነት እየተሳተፉበት መሆኑ ትልቅ ኩራት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

‎​የሰውን ልጅ የዝግመተ ለውጥ ታሪክ የለወጠችው የ3.2 ሚሊዮን ዓመቷ ድንቅነሽ መገኘት የሰውን ልጅ ምንነት ለመረዳት ትልቅ በር የከፈተ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበ ያለው ስኬት ግን የሐሰት የደህንነት ስሜት እንደፈጠረበት ፕሮፌሰሩ አስገንዝበዋል። የሰው ልጅ ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠርና ከተፈጥሮ ዓለም በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰቡ ስህተት መሆኑን በማንሳት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ስነ-ምህዳር መውደም በፕላኔቷ ላይ ከፍተኛ ስጋት እየደቀነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

‎በመጨረሻም፣ የሰው ልጅ የወደፊት ህልውናና ስኬት ዛሬ በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ጆሃንሰን፣ እኛ የዚህች ምድር ጠባቂዎች በመሆናችን የምንመካባቸውን ስነ-ምህዳሮች ማውደማችንን አቁመን ለዘላቂነት ትኩረት ልንሰጥ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

‎ጌትነት ተመስገን
(ከጎንደር ከተማ)
‎Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2