🙏
የመጀመሪያውና ታላቁ በደል ጥንተ አብሶ ሲሆን ቅዱስ ቄርሎስ “ጥንተ ኃጢአት” ቅዱስ ሳዊሮስና ቅዱስ ኤፍሬም “የቀደመው መርገም” ብለውታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው” እንዳለ ይህ የውርስ ኃጢአት ከአዳም ጀምሮ ከወላጅ ወደ ልጅ እየተላለፈ አዳምና ሔዋን ብቻ ሳይሆኑ ከእነርሱ የተወለዱ ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው ሁሉ በደለኞች ሆኑ፡፡ የሰው ባሕርየ ጐሰቈለ፣ ኃጢአት ብዙዎችን አጠመደች፡፡ ስለዚህም ተላልፈው ለሞትና ለሲኦል ተሰጡ። ከዚህ ንጽህት ሆና የተገኘች ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡ በኃጢትም ምክንያት በሰው ላይ ጸንቶ የነበረውን መርገም ሊያጠፋ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሰው ሆኖ በሚጸነስበት ልክና ሥርዓት ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወለደ። ለመወለዱ ዘርዕ ምክንያት አልሆነውም፤ በንጽሕና በቅድስና ጸንታ ከኖረች ከድንግል ያለአባት ተፀነሰ፤ ሕማም ድካም ሳያገኛት በሴቶች የሚደርሰውም ሳይደርስባት ተወለደ እንጂ።
ፍጹም ጌታ ፍጽምት በሆነች በእመቤታችን ማኅፀን አደረ፣ ቡሩክ አምላክ “ከሴቶች ይልቅ አንቺ ቡርክት ነሽ” ተብላ በመልአኩና በኤልሳቤጥ አንደበት ከተመሰገነች ከድንግል ተወለደ፤ ቡርክት ማኅፀን የቡሩክ አምላክ ማደሪያ ሆነች፡ ቅድስት ማኅፀን ቅዱስ ጌታን በሥጋ አስገኘች፤ ከመርገም በፊት ከነበረች ቡርክት ምድር አዳም ያለእናት ያለአባት ተፈጠረ፤ ዳግማይ አዳም ክርስቶስም ኃጢአተ አዳም ከሌለባት ቡርክት ማርያም ተወለደ፤ ከድንግል የተወለደ ጌታ ነውር ነቀፋ የሌለበት ንጹህ እንደሆነ፣ የወለደችው ድንግልም ነውር ነቀፋ የሌለባት ንጽህት ናት፤ እርሱ ለዘለዓለም ቅዱስ እንደሆነ እርሷም በጊዜ ሁሉ ቅድስት ናት፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው 35÷12 “መጀመሪያ የሌለው እርሱ አደፍ ጉድፍ የሌለባት ንጽህት ከሆነች ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም የነሣውን መገኛ ያለውን የሥጋ ባሕርይ ተዋሀደ” ይለናል፡፡
ሌላው ታላቅ አባት ቅዱስ ዲዮናስዮስ በዚሁ መጽሐፍ 101÷14 “አምላክን የወለደች አደፍ ጉድፍ የሌለባት ንጽህት በሆነች በድንግልማርያም ማኅፀን አደረ” መሆኗን ይነግረናል፡፡ ከድንግል የተወለደ ክርስቶስ ኢየሱስ በሰው የተፈረደውን መከራ ተቀብሎ ሰውን ለማዳን ሰው ቢሆንም ቅሉ ዕድፈት ርኲሰት ያላገኘው ንጹህ ቅዱስ እንደሆነ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምም እድፈት ርኲሰት የሌለባት ንጽህት ቅድስት መሆኗን እንረዳለን። በባሕርየ መለኮቱ ጽድቅ እንጂ ኃጢአት፣ ሕያውነት እንጂ መዋቲነት የማይስማማው አምላክ እናት ትሆነው ዘንድ ከሴቶች መካከል መርጦ፣ ትህትናን እንደ ዝናር አስታጥቆ፣ ንጽህናን እንደ አክሊል አቀዳጅቶ፣ ካዘጋጃት ከቅድስት እናቱ ነፍስና ሥጋን ነሣ፡፡
የነሣውንም ሥጋ በተዋህዶ ከባሕርየ መለኮቱ ጋር አንድ አደረገው። ሥጋን ተዋህዶ ስለተወለደ ግን በባሕርየ ሰብእ ፀንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ አላገኘውም፤ ድንግልም ኃጢአተ አበው የሚቆራኘው ተራ ሰውን የወለደች አይደለችም፡፡ የዚህ ዓለም ርኲሰት እንዳያገኛት ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የጠበቃት ንጽህት እንደመሆኗ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሳለው ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ተብሎ የሚመሰገን የቅድስናው መጠን የንጽህናው ልክ የማይሰፈር የማይለካ ፍጹም ጌታን ወለደች እንጂ። ይህን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን ያመኑ ገዳማውያን አባቶችም በየዕለቱ ሰዓሊ ለነ ቅድስት ይሏታል፤ ልቡናቸው በጎ ነገርን ስለሷ ይናገራል፡፡ ገዳማቸውን በመደገፍ በዓታቸውን በማጽናት የረድኤታቸው ተሳታፊ እንሁን፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
Source: Yeneta Tube









No comments yet.