አሸናፊዎቹ ወደ ካናዳ ያመራሉ!
#Fastmereja I የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከጆርካ ኢቨንትስ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና ከ200 በላይ ድንቅ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተጠናቋል።
ከሰኔ 17 ቀን ጀምሮ ሲካሄድ የቆየዉ ይህ ታላቅ ብሔራዊ ውድድር፣ ዛሬ በተደረገው ማራኪና አጓጊ የጎዳና ላይ ፉክክር ፍጻሜውን አግኝቷል።
ይህ ውድድር በካናዳ ሞንትሪያል ለሚካሄደው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና (ሀCI) ላይ ሀገራችንን ወክለው የሚሳተፉ ምርጥ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የተደረገ ዋና መድረክ በመሆኑ በከፍተኛ የፉክክር መንፈስ የተከናወነ ሲሆን፣ ዛሬ በወንዶችም በሴቶችም አሸናፊ የሆኑት ስፖርተኞች ወደ ካናዳ የሚያመሩ ይሆናል።
ዛሬ ረፋድ ላይ መነሻውን ቦሌ ኤድናሞል (ከሸገር ሕንፃ አጠገብ) አድርጎ በተካሄደው የፍጻሜ ውድድር ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርየስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መክዩ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌደሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ሐይሌ፣ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ኃላፊዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስፍራው ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል።
እልህ አስጨራሽ በነበረውና 80 ኪሎ ሜትር በሸፈነው የሴቶች ኤሊት የመንገድ ውድድር፣ በተለይም የመጨረሻዎቹን ሦስት ዙሮች ብቻዋን በሰፊ ልዩነት በመምራት ብስክሌተኛዋ ቤተልሔም ዳንኤል አንደኛ በመሆን ዉድድሩን አጠናቃለች።
በሌላ በኩል፣ 140 ኪሎ ሜትር በሸፈነውና ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት የወንዶች ኤሊት የመንገድ ውድድር ብስክሌተኛው ፊሊሞን ዘርአ ብሩክ ተፎካካሪዎቹን በብቃት በመቅደም በአንደኝነት አጠናቋል።
ባለፉት ዓመታት በተደረጉ መሰል ብሔራዊ ሻምፒዮናዎች ላይ የተገኙ ውጤቶች ስፖርተኞቻችን በጀርመን እና በቻይና ፕሮፌሽናል ክለቦችን እንዲቀላቀሉ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፣ የዛሬው ውድድርም ለአሸናፊዎቹ የዓለም ሻምፒዮና በርከመክፈቱ ባሻገር ለቀጣይ ዓለም አቀፍ የፕሮፌሽናል ዕድሎች ትልቅ መሠረት እንደሚሆን ተጠቅሷል።
በውድድሩ ማጠቃለያ ላይም ለዚህ ታላቅ ብሔራዊ ስፖርታዊ ኩነት መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የተለያዩ አካላትና ደጋፊዎች የምስጋና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።



Source: FastMereja









No comments yet.