በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብፁዕ አባ ሄኖክ አባታዊ ጥሪ አቀረቡ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I በደቡብ አፍሪካ በተለያዩ ከተሞች በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቀሰቀሱ ወቅታዊ ውጥረቶችና በሀገሪቱ ዜጎች በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ተከትሎ፣ የደቡብ አፍሪካና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ሄኖክ አስቸኳይ የአባታዊ ጥንቃቄና የጽናት መልዕክት አስተላለፉ።

በደቡብ አፍሪካ በተፈጠሩ ወቅታዊ ውጥረቶች እና ከሀገር እንድትወጡ በሚሉ ሰልፎች ምክንያት ወገኖቻችን በከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ውስጥ እንዳሉ እንረዳለን ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ተፈታኝ በሆነው ማዕበል ውስጥ የማይናወጥ መጠጊያ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል እንዲጸኑና ልባቸው በፍርሃት እንዳይናወጥ ጥሪ አቅርበዋል። ወቅቱ ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥበት የፈተና ጊዜ መሆኑን በማስታወስ፣ ምዕመናን በመንፈሳዊ ጥንካሬና በጸሎት ወደ ፈጣሪ እንዲጠጉ አሳስበዋል።

ብፁዕ አባ ሄኖክ በስደት ላይ የሚገኙ ወገኖች አሁን ላይ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን የሚገቡ አራት ዋና ዋና የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንደሚከተለው አደራ ብለዋል፦

ውጥረቶችና ሰልፎች በሚበራከቱባቸው አካባቢዎችና የንግድ ማዕከላት ያለ በቂ ምክንያት ከመንቀሳቀስ መቆጠብና በተለይም በምሽት ሰዓት እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት።

የአካባቢውን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ፣ ከኤምባሲም ሆነ ከማኅበረሰብ መሪዎች የሚወጡ ይፋዊ መግለጫዎችንና የደኅንነት ማስጠንቀቂያዎችን በንቃት መከታተል።

ከሌሎች ወገኖችና ከቅርብ ጓደኞች ጋር ያለውን የመረጃ ልውውጥ ማጠናከርና ድንገተኛ አደጋ ቢከሰት እንኳ በፍጥነት የሚደርስ የሰንሰለት መረጃዎችን መዘርጋት።

በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በአካል ከሚደረጉ አላስፈላጊ ክርክሮችና ግጭትን ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ አነቃቂ ሁኔታዎች ራስን ማራቅና በትዕግሥት መጠበቅ።

ሊቀ ጳጳሱ በደቡብ አፍሪካና በምዕራብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ እግዚአብሔር መከራውን አሻግሮ የፀጥታና የማረፍ ጊዜ እንዲሰጥ በመጸለይ ኢትዮጵያን፣ ደቡብ አፍሪካንና ምዕራብ አፍሪካን ባርከዋል።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: