የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
የግል ተበዳይ፤ አዲና ሁሴን የተባለን በግ አራጅ በመኖሪያ ቤታቸው በግ እንዲያርድላቸው ይስማማሉ፡፡ ግለሰቡም በስምምነታቸው መሰረት በጉን ካረደ በኋላ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ የነበረን 80ሺህ ብር የሚያወጣ አይፎን ፕሮማክስ ስልክ ሰርቆ ይሰወራል።
የስልካቸውን መሰረቅ ያረጋገጡት የግል ተበዳይም በልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ለመካኒሳ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት የጠፋውን ስልክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ፖሊስ ገልጿል፡፡
በክትትሉም የተሰረቀው ስልክ ከአንድ የሞባይል ጥገና ቤት ውስጥ ከእነ ተቀባዩ በቁጥጥር ስር ሊያውልም ችሏል፡፡
መሰል የወንጀል ድርጊቶች ያሉንን መልካም መስተጋብሮች የሚያጠፉ በመሆናቸው ልንከላከላቸው ይገባል ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ማምለጥ እንደማይችል በመረዳት ከወንጀል መታቀብ እንደሚገባውም አሳስቧል፡፡
Source: FastMereja









No comments yet.